የከተማዋ ነዋሪዎች የስራ አስፈጻሚውን ውሳኔ እንቃወማለን አሉ

70
መቀሌ ሰኔ 8/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ የአልጀርሱን ስምምነት  ሙሉ በሙሉ ለመቀበል ያስተላለፈውን ውሳኔ  እንደማይደግፉ የዓዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። ነዋሪዎቹ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት ትላንት ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ነው። ከሰልፈኞቹ መካከል የከተማዋ ነዋሪ  አቶ ወልደገብሪኤል ወልደማርያም በሰጡት አስተያየት "የኢህአደግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ የህዝቡን የመወሰን ስልጣን ወደ ጎን የተወ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም "ብለዋል። የዓዲግራት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰንበቱ ባራኪ በሰጡት አስተያየት ውሳኔውን  እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ " የድንበር ችግር በሁለቱም ሃገራት ህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ስራ ነው መፈታት የሚገባው" ያሉት ደግሞ  አቶ ተስፋዬ ኃይሉ ናቸው። " ችግሮቻችንን የሁለቱም ሃገራት ህዝቦች በጋራና በመስማማት እንፈተዋለን" ሲሉም በሰልፉ ላይ ባሰሙት መፈክር ገልፀዋል፡፡ የአዲግራት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገብረመድህን ስዩም  ለሰልፈኞቹ በሰጡት ምላሽ ፤ህዝቡ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ  እንዲያገኝ ለሚመለከተው አካል እንደሚያደርሱ ገልጸውሏቸዋል። በዓዲግራት ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም