ወርቅ የዋጠው ዶሮ  

797

ጳጉሜ 5/2011 ለሽያጭ ገበያ የወጣው ዶሮ 1 ነጥብ 75 ግራም የሚመዝን የጆሮ ጌጥ ወርቅ  ይውጣል።

ነገሩ የተከሰተው ጳጉሜ 03 ቀን 2011 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ነው፡፡

ባለቤትነቱ የአቶ ደነቀ ሸለመ የሆነው ዶሮ ለሽያጭ ገበያ ወጥቶ ገዢዎችን በመጠባበቅ ላይ እንዳለ የወይዘሮ ሃጫልቱ በድሩን 1 ነጥብ 75 ግራም የሚመዝን የጆሮ ጌጥ ላይ አነጣጥሮ ከጆሮዋ ላይ በጥሶ ይውጣል።

ነገሩ ከተከሰተ በኋላ  የዶሮው ባለቤትና የወርቋ ባለቤት ሰጣ ገባ ውስጥ ይገባሉ፡፡

የወርቋ ባለቤት ወይዘሮ ሃጫልቱ ዶሮው ወዲያው ታርዶ ወርቃቸው እንዲሰጣቸው ቢሹም የዶሮው ባለቤት ደግሞ  በጉዳዩ አልተስማሙም።

ነገሩ መክረሩን ያዩት ገቢያተኞች ጉዳዩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ በማድረግ በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኝ የወሊሶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ያመራሉ፡፡

ጉዳዩ እንግዳ የሆነበት የወሊሶ ከተማ አስተዳዳር ፖሊስ ጣቢያም ጉዳያቸውን በመስማማት እንዲፈቱ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል።

የዶሮው ባላቤትም ወይዘሮ ሃጫልቱ ዶሮው የሚያወጣውን ዋጋ ከፍለው ዶሮውን ይረከቡኝ ሲሉ ይስማማሉ።

አቶ ደነቅም የወርቁ ባለቤት 250 ብር እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም ባለ ወርቋ የተጠየቀውን ብር የለኝም በማለታቸው 150 ብር ሰጥተዋቸው ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፈታቱን ነው  የወሊሶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሃላፊ ኮማንደር ከበደ በዳዳ የተናገሩት።