ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ተገለፀ

72
አሶሳ ኢዜአ ጳጉሜ 5 / 2011 በአሶሳ ከተማ የበዓል ወቅትን ጨምሮ በየጊዜው በሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚደረገው ምክንያት የሌላው የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ በአሶሳ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበዛሽ ይርጋ እንዳሉት የዘመን መለወጫ በዓል መቃረቡን ተከትሎ በአብዛኛው ምርቶች እና ሸቀጦች ላይ ጭማሪ እየታየባቸው ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ቀይ ሽንኩርት 25 ፣ ነጭ ሽንኩር 170 ብር፣ ለጋ ቅቤ 250 ብር፣ ፍርኖ ዱቄት 40 ብር፣ አተር 50 ብር በኪሎ ሲሸጡ አንድ እንቁላል ስድስት ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በተጠቀሱት ሸቀጦች ላይ በኪሎ ከአምስት እስከ 15 ብር ጭማሪ እንደታየባቸው ገልጸዋል፡፡ ዶሮ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ኢብራሂ ሠይድ የአንድ ከፍተኛ ዶሮ ዋጋ እስከ 250 ብር ሲሆን ከሰሞኑ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የ50 ብር ያህል ጭማሪ ታይቶበታል ይላሉ፡፡ አብዛኞቹ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ሸቀጣ ሸቀጦች በአካባቢው የሚመረቱ እንደሆኑ የሚናሩት ስተያየት ሰጪዎቹ የዋጋ ጭማሪው በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እያማረረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የአካባቢው ሠላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በከተማው በዓልን ጨምሮ በየጊዜው የሚደረገው ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ተገቢው ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ በመስኖ ያመረተውን ነጭ ሽንኩርት በኪሎ እስከ 170 ብር እየሸጠ እንደሆነ የሚናገረው በአሶሳ ወረዳ የመገሌ 23 ቀበሌ ወጣት አዳነ ንጋቱ ነው፡፡ አሁን አንድ ኪሎ ሽንኩርት እየሸጠ የሚገኝበት ዋጋ ለዘር፣ ለትራንስፖርት እና ምርቱን ለማግኝት በሚሠራበት ወቅት ካፈሰሰው ጉልበት አንጻር ተመጣጣኝ ነው ይላል፡፡ ከወራት በፊት አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩር በ60 ብር እንደሸጠ ያስታውሳል፡፡ ለከተማው የሚቀርቡ በርካታ ሸቀጦች ከሩቅ አካባቢ የሚመጡበት ወቅት እንዳለ ጠቅሶ ወጣቶችን በስፋት በመስኖ ማሠማራት ቢቻል ገበያን ማረጋጋት እንደሚቻል ያምናል፡፡ በአሶሳ ከተማ ቅዳሜ ገበያ የእህል በረንዳ ባለቤት አቶ ወልደሚካኤል ሃጎስ እንደሚሉት ከጤፍ በስተቀር በፍርኖ ዱቄት፣ ምሥር፣ አተር እና ሌሎችም የጥራጥሬ ሰብሎች ላይ ሰሞኑን በኪሎ እስከ አምስት ብር ጭማሪ መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ሸቀጦቹን እና ሰብሎቹን በግዥ ከሚያስመጡባቸው አካባቢዎች ጭማሪ በመደረጉ እርሳቸውም ለመጨመር መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ሠይድ ዓሊ በክልሉ በተለይ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በበርካታ መሠረታዊ ምርቶች እና ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ምርቱን በማከማቸት እጥረት ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት መሆኑን ገልፀው ህገ-ወጥ ደለሎችም ዋጋ እንዲንር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡ ይህም የፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን እንዲከሰት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ በከተማው የሚገኙ ሁሉንም የንግድ ማህበረሰብ በማሰባሰብ በጉዳዩ ላይ ለማወያየት እንደተሞከረ ጠቅሰው በህገ-ወጦች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ከአሶሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከሚወሰደው እርምጃ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ የሸማቾች ማህበራትን አቅም በማደራጀት እህልና መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም በተለይ ጤፍን ጨምሮ የሰብል ዋጋን ለማረጋጋት መቻሉን ጠቁመው ይኸው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሠይድ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም