“ሱዳንን ከአሜሪካ የሽብር መዝገብ ማሰረዝ ቀዳሚው የትኩረት ስራዬ ነው”- አስማ አብደላ

89

ጳጉሜ 4/2011 የሱዳን የመጀመሪያዋ ሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማ አብደላ ወደ ስልጣን ከመጡ ገና 24 ሰዓት ቢሆናቸውም በቀጣይ ስራቸው ሀገራቸውን ከአሜሪካ ሽብርን የሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ማሰረዝ ቀዳሚው ስራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፥ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሱዳንን ከሽብር መዝግብ በማሰረዝ ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት አቅደዋል።

ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከተያዙት አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፥ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ውይይቶች በማድረግ እንደሚፈታ ተስፋ አድርገዋል።

አሜሪካ በፈረንጆቹ 1993 ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ማካተቷ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሱዳን በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ላይ ስትሆን፥ የውጭ ኢንቨስትመንትም ቀንሶባታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ባለፈው ወር እንዳሉት ዋሽንግተን ካርቱምን ከሽብር መዝገቧ ለመሰረዝ ገና ብዙ ስራዎች ይቀራሉ።

ሱዳን የሰብዓዊ መብት መከበር፣ የሃይማኖት ነጻነት፣ ሽብርን የመከላከል ስራዎች እና ውስጣዊ ሰላምን ማስፈን ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ ዴቪድ ሃሌ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም