ኢትዮጵያዊያን የኩራታቸው ምንጭ የሆነውን ህብረብሄራዊ አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር መስራት አለባቸው ተባለ - ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም

92
ጷጉሜ 3/2011 "ኢትዮጵያዊያን የኩራታቸው ምንጭ የሆነውን ህብረብሄራዊ አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ጠንክረው መስራት አለባቸው" ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም አሳሰቡ። አፈ ጉባኤዋ ማሳሰቢያውን የሰጡት ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የተከበረውን ብሄራዊ የኩራት ቀን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ውይይቱን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ምሁራንንና ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎት ታድመውታል። የፌዴሬሽን ምክር  ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኪሪያ ኢብራሂም በዚሁ ወቅት የገናና ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያውያ ዜጎች ተከባበረውና ተደጋግፈው ማደግ የሚችሉ፤ ይህንንም በተግባር ለዓለም ህዝብ ያሳዩ ታላቅ ህዝቦች ናቸው ብለዋል። አክለውም "አንዱ ብሄር ለሌላው ብሄር ኩራት ነው"  ያሉት አፈጉባዔዋ፤ "አንዱ ሀይማኖትም ለሌላው ኩራትና ክብሩ ነው፤ ስጋት የሚሆንብን ማንነት ወይም ብሄር ከቶ የለንም" ሲሉም ተናግረዋል። ብሄራዊ የኩራት ቀን ሲከበርም ሁሌም የሚያኮራ እንዲሆን ዜጎች በመከባበርና በመቻቻል አገሪቱን ወደሚፈለገው የእድገት ከፍታ ለማውጣት መጣር ይገባልም ሲሉ መክረዋል። በተለይም የሁሉም ኢትዮጵያዊ የኩራት ምንጭ የሆነውን ህብረብሄራዊ አንድነት ይበልጥ ማጠናከር ይገባልም ብለዋል። የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ብሄራዊ የኩራት ቀንን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፣ የአርበኛና የጎሰኛ ኩራትን መለየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። "የአርበኛ ኩራት ማለት የራሱን የሚወድ፣ በራሱ አገር የሚተማመን ሲሆን የጎሰኛ ኩራት ማለት እራሱን  ከሌላው ጋር እያወዳደረ ሌላውን የሚጠላ ነው" በማለት ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያስቀጥል አገራዊ ኩራት መከተል በእጅጉ የሚመረጠው ነው ብለዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ ነጻነት ጀምበር በሰጡት አስተያየት እለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ባለ መልኩ መታሰቡ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር ሌላ አዲስ ምዕራፍ ነው ሲሉ ገልፀዋል። የአሁኑ ትውልድ የቀደሙት አባቶች ጠብቀው ያቆዩዋቸውንና የኢትዮጵያ መለያ ኩራት የሆኑ ታሪኮችንና ቅርሶችን  ለተከታዩ ትውልድ የማቆየት ኃላፊነት እንዳለበትም ወይዘሮ ነፃነት አሳስበዋል። ወይዘሮ ብርሃኔ ፅምሩ በበኩላቸው፣ "የትላንት ትውልዶች ባኖሩት ታሪክና ስራ በመኩራት እለቱን ማክበር  ባይከፋም ፣ ዛሬ ላይ ያለችዋ ኢትዮጵያ በኩራት እንድትቀጥል ግን በርካታ መሰራት ያለባችው ተግባራት አሉ" ነው ያሉት። የተለያዩ ምሁራን በመድረኩ ላይ ሀሳባቸውን የገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ኩራት እንዴት ማምጣትና ማስቀጠል እንደሚቻልም ውይይት ተደርጓል። ጳጉሜ 3 ቀን ብሄራዊ የኩራት ቀን ማለዳ ላይ በመስቀል አደባባይ በተለያዩ ትዕይንቶች በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎቸ በተገኙነት የተከበረ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከሰዓት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም