የእስልምና እምነት ተከታዮች በፆሙ ወቅት ያሳዩትን መልካም ስነምግባር በቀጣይም እንዲፈጽሙት ተጠየቀ

79
ሀዋሳ ሰኔ 7/2010 የእስልምና እምነት ተከታዮች በረመዳን ፆም ወቅት ያሳዩትን መልካም ስነምግባር በቀጣይም እንዲፈጽሙት የደቡብ ህዝቦች ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጠየቀ፡፡ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሀጂ አህባብ አባጀማል 1ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት "ለሰዎች ፍቅርን፣ ድጋፍን፣ ሰላምና እርቅ መስጠትና ማድረግ ያለብን በረማዳን ወቅት ብቻ ሳይሆን እድሜ ልካችን መሆን አለበት" ብለዋል፡፡ ለአለም፣ ለሀገርና ለሰላም ዱኣ ማድረግ የሚገባውም በፆም ጊዜ ብቻ ሳይሆን የዘውትር መንፈሳዊ ስራ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ትውልዱ ህገ መንገስቱን፤ ወላጆችውንና ታላላቆችን ማክበርና ሀገሩን መውደድ እንደሚገባውም አሳስበው "የኃይማኖቱ ተከታዮች ለሀገሪቱ ደህንትና ለሰላም ዘብ መቆም ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡ መንግስት በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እርቅ ማውረድና ይቅርታ የማድረግ ተግባሩ የሚበረታታ መልካም ተግባር እንደሆነ ያመለከቱት ሀጂ አህባብ፤ የእምነቱ ተከታዮች በራማዳን ፆም ወቅት ያሳዩትን መልካም ስነምግር እንዲቀጥሉበት ጠይቀዋል፡፡ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱና እስረኞችን ነፃ እንዲወጡ እየተደረገ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ልዩነት ቢኖርም በመቻቻል፣ በመከባበርና በአንድነት ተሳስቦ መኖር እንደሚገባ መክረዋል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ከተቸገሩ ወገኖችና ከተለያዩ እምነት ተከታዮች ጋር እንዲያከብሩም ጠይቀዋል፡፡ ለእስልምና እምነት ተከታዮች፣ ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ1ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝደንት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም