ብአዴን የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ

60
ደሴ ሰኔ 7/2010 የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ  የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡ በምስራቅ አማራ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የድርጅት አመራሮች በተገኙበት የብአዴን ድርጅታዊ የግምገማ መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡ የብአዴን ስራ አስፈፃሚ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም የህዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አሁንም ክፍተት አለ፡፡ ከዚህ በፊት በአባላትና በአመራሩ መካከል የአድርባይነት መንፈስ ስለነበር ድርጅቱ በመርህ ላይ ተመስርቶ እንዳይታገልና ለውስጥ ችግሮች እንዲጋለጥ አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ ግን የልማትና የዴሞክራሲ መስመሩን በማስቀጠል የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ለመፍታት መግባባት ላይ እንዳደረሳቸው አስረድተዋል፡፡ "ይህም የድርጅቱን ጥንካሬ በማጎልበት ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት በተግባር ለመለወጥ የሚያስችለው ነው" ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የአማራ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የጥላቻንና የመጠራጠርን መንፈስ በመስበር የአንድነት አስተሳሰብ እየጎለበተ በመምጣቱ በህዝቡና በድርጅቱ መካከል መተማመን እየተፈጠረ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ እድገቱን ማስቀጠል ቢቻልም መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት የህዝቡን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ግን ውስንነት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ 26 ነጥብ 5 በመቶው ከድህነት ወለል በታች እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ብናልፍ የኑሮ ውድነትንና ስራ አጥነትን ማስወገድና ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የድርጅቱ ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን የመቅደላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቆያቸው አያሌው በበኩላቸው በየደረጃው ያለው አመራር ህዝብን በማገልገል ረገድ ውስንነት እንደነበረበት በጥልቅ ተሃድሶው መለየቱን ገልፀዋል፡፡ ችግሩን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት ባለሙያው በተረጋጋ መንፈስ አገልግሎት የመስጠት፣ አመራሩም ለተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት አቅም እያጎለበተ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡ የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመስ በተደረገው ጥረት ዘንድሮ በስምንት ቀበሌዎች አዲስ የገጠር መንገድ በመክፈት እናቶች የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲያገኙና አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ገልጸዋል፡፡ ከ76 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን በወረዳው አቅም መገንባቱን አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡ በወረዳው ውስጥ ካለው ሰፊ ችግር አንጸር የህዝቡን እርካታ የሚያረጋግጥ ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል። የደሴ ከተማ ብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ጀማል ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ የህዝቡን ጥያቄዎች የመመለስ ጅምር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በከተማዋ ህዝብ ዘንድ ችግርን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል በመጎልበቱ ቀደም ሲል በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት በከተማዋ አለመከሰቱን አመልክተዋል፡፡ በከተማዋ የመልካም አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን የገለፁት አቶ መሐመድ የተወሰኑትን ለመፍታት ቢሞከርም ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ጥረቱ የህዝቡን እርካታ የሚያረጋግጥ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ ችግሮቹን ለመፍታት ከህዝቡ፣ ከአመራሩና ከአባሉ ጋር በተደረጉ ውይይቶች መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡ ከጽዳት፣ ከስራ አጥነት ቅነሳ፣ ከህገ ወጥ ተግባራት ቁጥጥር ጋር በተያያዙም በስፋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን የቡግና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለምዬ ሽበሽ በበኩላቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች በአካባቢው ለተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ዋነኛ ምክንያቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ አመራሩ ይሄን ችግር ለመቅረፍ ባደረገው ጥረት ተስፋ ሰጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ያለው ምስራቅ አማራ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የድርጅት አመራሮች ድርጅታዊ ግምገማ መድረክ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም