የኮትቻ አፈርን በዘመናዊ መልክ አንጣፈን ማልማታችን የምግብ ክፍተታችንን እንድንሞላ አግዞናል አርሶ --አደሮች

83
ጵጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ የጥቁር አፈር መሬትን በማንጠፈፍ ወደ ልማት እንዲገባ በመደረጉ የምግብ ክፍተታችንን ለመሙላት አግዞናል ሲሉ የምስራቅና ምዕራብ ጎጃም አርሶ አደሮች ገለጹ። በክልሉ ከ316 ሺህ መሬት በላይ የጥቁር አፈር መሬት በዘመናዊና ባህላዊ ዘዴ በማንጣፈፍ በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑን የአማራ ግብርና ቢሮ ገልጿል። አርሶ አደሮቹ እንደተናገሩት የጥቁር አፈር መሬትን በባለሙያ ታግዘን በማንጣፈፍ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማልማት የተሻለ ምርት እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል ። በምስራቅ ጎጃም ዞን በእናርጅ እናውጋ ወረዳ መጣያ እንዳራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር እናውጋው ባየ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውሃ የሚተኛበትን ጥቁር አፈር መሬት አንጣፈው በሰብል በማልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ይናገራሉ ። ውሃ የሚተኛበት ግማሽ ሄክታር መሬታቸው ዘመናዊ የእርሻ ማረሻ መሳሪያዎች ተጠቅመው በማንጣፈፍ በክረምቱ ወቅት በስንዴና በገብስ ሰብሎች በመሸፈን እስከ 16 ኩንታል ተጨማሪ ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል። መሬቱ ቀደም ሲል እርጥበትን ተጠቅመው ከሚያለሙት የጓያ ሰብል በስተቀር መሬቱ በክረምት ወቅት ውሃ ስለሚተኛበት ምርት አይሰጥም ነበር ብለዋል ። አሁን ግን በክረምት ወቅትም ሆነ ክረምቱ ከወጣ በኋላ ቀሪ እርጥበትን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ በማልማት የተሻለ ምርት ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። በዚሁ ወረዳ የጎል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙንየ አንተዬ በበኩላቸው የጥቁር አፈር መሬት በክረምት ወቅት በውሃ ተሸፍኖ መክረም በባለሙያዎች ድጋፍ ታሪክ አድርገናዋል ይላሉ ። በግብርና ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ መሬቱን በቢቢኤም መሳሪያ ውሃውን ከማሳው በማስወጣት ሁለት ጊዜ ምርት እንዲሰጥ ማድረግ መቻላቸውን ተናግረዋል። የጥቁር አፈር መሬታቸው በክረምት ወቅት በአራሙቻ ተወሮ ይከርም እንደነበር የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢጠህናን ወረዳ የሆድ አንሺ ጋተጎን ቀበሌ አርሶ አደር ይታየው ብርሃን ናቸው። የተሻሻሉ የእርሻ ማረሻዎችን በመጠቀም መሬቱን አንጣፍፈው በቆሎ፣ ገብስና ስንዴ በማልማት ከ30 ኩንታል በላይ ምርት እያገኙ ለመጠቀም  አስችሎአቸዋል። ክረምቱ ሲወጣ ደግሞ መሬቱን በሽንብራ ሰብል ዳግም በማልማት እስከ 12 ኩንታል የሚደርስ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም ተናግረዋል። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው መሬታቸውን አንጣፈው ማልማት በመጀመራቸው በሰብል ምርት የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት ከመሙላት አልፈው ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን አስረድተዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አቶ አቢዮት መኮንን እንደገለፁት በዚህ የመኽር ወቅት 316 ሺህ 400 ሄክታር የጥቁር አፈር መሬት በዘመናዊና ባህላዊ ዘዴ ተንጣፍፎ በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን ተናግረዋል። በተግባር የተደገፈ ስልጠና ለአርሶ አደሩ በመሰጠቱ በክረምት ወቅት በአብዛኛው ውሃ ተኝቶ ይከርምበት የነበረውን የኮትቻ መሬት  በዘመናዊ ዘዴ አንጣፎ በመዝራት ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል። በክልሉ የጥቁር አፈር መሬትን በማንጣፈፍ ልማት 416 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቅሰው በስንዴ፣ በገብስና በቦለቄ ከለማው መሬትም 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል ። በልማቱ ለተሳተፉት አርሶ አደሮችም 3 ሺህ 595 የተሻሻሉ የእርሻ ማረሻዎች ተሰራጭቷል። በክልሉ ባለፈው የመኽር አዝመራም  ተንጣፍፎ ከለማው 321 ሺህ ሄክታር የኮትቻ መሬት 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቦ እንደነበር ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም