ህዝብ ግንኙነቶች መረጃ በጥራትና በፍላጎት መስጠት ላይ ችግር አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 መረጃን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በነፃነት መስጠትና ከሚዲያ ጋር በትስስር መስራት ላይ የህዝብ ግንኙነት አካላት ክፍተት እንዳለባቸው ተገለፀ። በፌደራል ደረጃ ከ130 በላይ የህዝብ ግንኙነት ዘርፎች ያሉ ቢሆንም የመረጃ ነፃነትን በሚያመላክት መልኩ አብዛኛዎቹ የቃል አቀባይነት ስራቸውን በኃላፊነት እየሰሩ አለመሆናቸው ተጠቁሟል። ተቋማት ለህዝቡና ለሚዲያ አካላት መረጃን የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ቢደነግግም፤ በዚያ ልክ ሚዛናዊ መረጃን ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑ የህዝብ ግንኙነት አካላት መኖራቸውን ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው በዘርፉ ያሉ አካላት ያስረዱት። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገዛሃኝ አባተ "ባለሙያዎች ሚዛናዊና ጠቃሚ መረጃዎችን በህብረተሰቡ ፍላጎት ልክ መስጠት አለባቸው" ይላሉ። ሆኖም ከዚህ አንፃር ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን ነው የግብርናና የእንስሳት ሃብት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ብርሃኑ የተናገሩት። መረጃ መስጠት ግዴታቸው መሆኑን የማይረዱ አንዳንድ ባለሙያዎች እንዳሉም አሳውቀዋል። የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች  ለሚዲያ አካላትም ጭምር መረጃ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው ነው የሚዲያ አካላት የገለጹት። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይረክተር አቶ ሰይፈ ደርቤ እንዳሉት ለህብረተሰቡም ለተቋማቸውም ቅርብ የሆኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ቢኖሩም ተፈላጊውን መረጃ ለህዝብም ለመገናኛ ብዙሀንም ለመስጠት አይፈልጉም፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አቤል አዳሙ እንዳሉት ደግሞ ባለሙያዎቹ ሲፈልጉ ወደ መገናኛ ብዙኃን ይመጣሉ እንጂ ለሚፈልጓቸው መገናኛ ብዙኃን  መረጃ የመስጠት ፍላጎት የላቸውም፡፡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በሮቻቸውን ክፍት ማድረግ እንዳለባቸው የጠቆሙት ምክትል ስራ አስኪጁ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የተግባቦት ባለሙያ እንደሚስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ ሌላ የሚሰጡ መረጃዎችም ሚዛናቸውን ያልጠበቁና ጥሩ አፈፃፀሞች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያስረዱት። ለክፍተቶቹ መፈጠር ከባለሙያው የተነሳሽነት ማነስ፣ የእውቀት ክፍተትና የሰው ኃይል እጥረት በተጨማሪ  የአደረጃጀት ክፍተቶችም ድርሻ እንዳላቸው ተጠቁሟል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው የአጠቃቀም፣ የክህሎትና የእውቀት እጥረት አንዳንዴም የመረጃ መጣረስን እያስከተለ መሆኑንም ነው የገለፁልን። እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት  የአቅም ግንባታነና የሪፎርም ስራዎች በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት እየተሰሩ እንደሆነም ተጠቁሟል። የጽሕፈት ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ተቋማቱ የህዝብ ቃል አቀባይ ሆነው ከመስራት አንፃር ብዙ ጉድለቶች የታዩ መሆኑን ገልፀው፤ ችግሮቹን ተራ በተራ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የተቋማትን የተቀናጀና ትክክለኛ መረጃ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግም ወቅቱ የሚፈልገውን ዘዴ መጠቀም ከባለሙያዎቹ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ አንፃርም ባለሙያዎቹ መረጃዎችን ያለምንም ንፍገት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም