የኢኮኖሚ ምሁራኑ ከወዴት አላችሁ?

58
በትንሳኤ ገመቹ ኢዜአ ዕለተ ረቡዕ ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት። ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በሸራተን ሆቴል ስንደርስ የመሰብሰቢያ አዳራሹ በመልክ በመልክ ተሰድረው ከተቀመጡ መቀመጫዎች ሌላ ተንቀሳቃሽ ፍጡር አልነበረም። ከጥቂት ቆይታ ኋላ እንደኛው ለስራ በቦታው የተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ጥቂት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ወደ አዳራሹ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እኛም መርሃ ግብሩ እስኪጀመር አዳራሹ አካባቢ ከወዲያ ወዲህ እያልን ማማተራችንን ተያይዘነዋል። መቼም የጋዜጠኛ ነገር አይኑም እግሩም አንድ ቦታ አይቀመጥም አይደል? እኔና የስራ ባልደረባዬ በተለይ እዚህ ቦታ ተመድበን ስንመጣ ለሌላ “’የዜና ዘገባ በመረጃ ሰጪነት ይተባበሩናል” ብለን ያሰብናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን እንደምናገኝ እርግጠኛ በመሆን ነበር። ለዚህም ነው ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ በተናጠልና በጋራ ሆነው የሚገቡ እንግዶችን ማንነት በአንክሮ የምንከታተለው። ከእንግዶቹ ውስጥ አብዛኞቹን ማወቅ ባያዳግተንም አልፎ አልፎ የማናውቃቸው ሰዎችን መጥተው ስንመለከት አስተባባሪዎችን መጠየቃችን አልቀረም። ወደ አዳራሹ ከመጣን ከአንድ ሰዓት በኋላ በስርዓት ተሰድረው የነበሩ መቀመጫዎች መሙላት ጀምረዋል። ከእንግዶቹ ወስጥም አብላጫውን ቁጥር የያዙት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባለት ሆነዋል። ጥቂት የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ ምሁራንና የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችም ቦታ ቦታቸውን በመያዝ የመርሃግብሩን መጀመር ይጠባበቃሉ። ከመድረክ ፊት ለፊት “አገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” የሚል ጽሁፍ ጎልቶ ይታያል። የዕለቱ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ወደ አዳራሹ መግባትን ተከትሎ የመድረኩ አስተባባሪ መርሃ ግብሩ መጀመሩን አበሰረ። የዚህ መድረክ ዓላማ እስካሁን በኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ረገድ የተገኘውን ስኬት የበለጠ ለማጠናከርና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ መዘጋጀቱንና በዚህ ሰነድ ላይ የባለድርሻ አካላትን አስተያየት በግብዓትነት ለመውሰድ መሆኑን በአዘጋጆቹ ተብራራ። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀና በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ  በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነዱ ላይ ያተኮረ የመክፈቻ ንግግር እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ መኮንን በሰነዱ ላይ ሰፊ ገለጻ ካደረጉ በኋላ ውይይቱ ተጀመረ። እኔም ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ የተነሳሁበት ፍሬ ነገይ ይህ ውይይት መሆኑን ልብ ይሏል። በመግቢያዬ እንደገለጽኩት እኔና የስራ ባልደረባዬ ወደዚህ ስንመጣ “እናገኛቸዋለን” ብለን ያሰብናቸውን የዜና ምንጮች የምንለይበት ሰዓት በመድረሱ ውይይቱን በጉጉት ነበር የምንጠብቀው። አቶ አህመድና ዶክተር እዮብ እንዲሁም የብሄራዊ ባንክ ገዥው ዶክተር ይናገር ደሴ ከተሳታፊዎች ለሚቀርቡ ጥያቀዎች መልስ በመስጠትና አስተያየት በመቀበል ተወጥረዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ተሳታፊዎች ለአስተያየት እድል ከመስጠታቸው በፊት ተሳታፊዎች ለሰነዱ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን በአጭሩ እንዲያቀርቡ፣ እያንዳንዱ አስተያየት ሰጪም ከዕውቀቱና ከልምዱ በመነሳት ሰነዱን ሊያዳብሩ የሚችሉ ሀሳቦች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማሳሰቢያ ጭምር ሰጥተዋል። መንግስት ለብቻው ምንም አይነት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነዶችን ቢያዘጋጅ የመላው ህብረተሰብ ተሳትፎና ተቀባይነት ከሌለው ከሰነድነት ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው በማንሳት። ውይይቱ በምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አስተያየት አንድ ብሎ ጀምሯል። አቶ ዘመዴነህ በሰነዱ ላይ የቀረበውን ማብራሪያ በማድነቅ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ጀመሩ። በሰነዱ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ የማምረቻ ኢንዱስትሪው ውስጥ በቀላሉ መግባት የሚያስችለው ሁኔታዎች ተመላክተዋል ወይ? የውጭ ባለሃብቱ በተወሰነ ደረጃ ከመንግስትና ከግል ባለሃብቱ ጋር በጥምረት በባንክ ስራ ላይ መሳተፍ የማይችሉትስ ለምንድን ነው? ሰነዱ ይህን ሊመልስ ይችላል ወይ? የከተማ ፖሊሲ አለ ወይ ከሌለስ ለምን አይወጣም? ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት የህዝብ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፤ ይህም በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያመጣ መሆኑ ለምን ትኩረት አልተሰጠውም? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት ድምጽ ማጉያውን ለሌላ ተረኛ አስረከቡ። ከምጣኔ ሃብት ባለሙያው አስተያየት በኋላ ከሁለት የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና አንድ ከግል ዘርፍ የመጣ ተሳታፊ ውጪ ተናጋሪ የነበሩት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ሆነዋል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ለምንድን ነው በመድረኩ ያልተገኙት? ጉዳዩ በዋናነት እነርሱን አይደል እንዴ የሚመለከተው? እኔና ባልደረባዬ መልስ ያላገኘንለት ጥያቄ ነበር። በእርግጥ ከመድረኩ አዘጋጆች የምጣኔ ሃብት ምሁራን እንደሚገኙ ተገልጾልን የነበረ ቢሆንም። ከኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲ ድርጅት የመጡት አቶ አድማሱ ሃይሉ የማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በሚቀረጽበት ጊዜ ዋነኛ መሰረቱ ስርዓት ነው፤ በየትኛው ስርዓት ላይ ቆመን ነው ይህን ማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ የምናደርገው? በማለት ይጠይቃሉ። ኢህአዴግ የሊበራል ፍልስፍናን እስካልተገበረ ድረስ የወደፊት ኢትዮጵያን መገንባት እንዴትስ ይቻላል? ይህም የእርሳቸው ጥያቄ ነው። ከኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር የመጡት አቶ ዑመር መሃመድ በበኩላቸው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማለት ምንድን ነው? በአገሪቷ ብዙ ማዕድናት አሉ ይህን ማውጣት ሳይቻል ለምን ስለዶላር ታስባላቹ? ግብርናውን ለምን አታሳድጉም? ለምን መሰረተ ልማት አላሟላችሁም? እነዚህን ሳትሰሩ የውጭ ዶላር ብቻ  እጥረት አለ ማለት ጠቃሚ አይደለም” የሚል በጥያቄ የተሞላ አስተያየት ሰጥተው በማመስገን ድምጽ ማጉያውን አስረከቡ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተረኛ አስተያየት ሰጪ ናቸው። እርሳቸውም እንዳሉት አገሪቷ እስካሁን ላስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለዚህ ደግሞ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የተደረገውም ጥረት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። ባለፉት 20 ዓመታት ሁለት ብቻ የነበረው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 50 መድረሳቸው ሳይደነቅ ሊታለፍ  አይገባም። ሰነዱ ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው ባለሙያ እንዲያፈሩ ተቋማቱ ላይ “ትኩረት ሊሰጥ ይገባል” በሚል አስተያየታቸውን አጠናቀቁ። ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ የመጡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሰጡት አስተያየት አጽንኦት የሰጡት በሰነዱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶች ለአብነት ሙስናና መልካም አስተዳደር መዘንጋቱን ነበር። ጎልተው ሊወጡ የሚገባቸው ጉዳዮች አልተዳሰሱም። የመሬት ባለይዞታነት ላይ ያሉ ችግሮችም መፍትሄ አልተሰጣቸውም ነው ያሉት። እንደርሳቸው አገላለጽ፤ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መስህቦችም ትኩረት አልተደረገባቸውም። በእጅ ያሉ ሃብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም። በአዲስ አበባ እንኳን የኤሌክትሪክ ሃይልና የውሃ አገልግሎቶችን ማዳረስ አዳጋች ሆኗል። በመሆኑን ያለውን ሃብት በአግባቡ በመጠቀም “ኢኮኖሚውን ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጉ” ብለዋል። ''ከአንድ ዓመት በኋላ ስልጣን ይለቃል ብለን የምንጠብቀው ኢህአዴግ የአስር ዓመት ዕቅድ ይዞ መምጣቱ ግርታ ፈጥሯል'' በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ የመጡት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። የአገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታ ካልተስተካከለ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማ አይሆንም። ብሄራዊ መግባባት ሳይፈጠር ትላልቅ እቅዶች ማቀድ ትርፉ ልፋት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በአሁን ወቅት በአገሪቷ “እኔ ብቻ” የሚል ስሜት እየጎላ መምጣቱንም አንስተዋል። ኢህአዴግ ሙስናናን ለማስቆም ቁርጠኛ አቋም አለማሳየቱ ደግሞ ለሰነዱ ውጤታማነት ስጋት እንደሆነ በመጥቀስ አስተያየታቸውን አጠናቀዋል። መድረኩ ላይ የተሰየሙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ከአስተያየቶቹ በኋላ አብዛኛውን ጥያቄ መመለስና እንደገና ሰነዱን ማብራራት ጀምረዋል። መንግስት የግል ዘርፉን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነና በሂደትም በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ እየቀነሰ የሚሄድበት አሰራር እንደሚዘረጋ  ማብራሪያ ተሰጥቷል። ዶክተር ይናገር በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማበረታታት የብድር አቅርቦትን ማመቻቸትና የውጭ ምንዛሬን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ላይ ቀደም ሲል ከነበረው አሰራር ማሻሻያ መደረጉን አስታውሰዋል። የውጭ ምንዛሬን ችግር ጨርሶ ማጥፋት ባንችልም የእጥረቱ ዋና መነሻ የሆነውን የአቅርቦት ችግር ለማቃለል ርብርብ እናደርጋለን ሲሉም ቃል ገብተዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፤ መንግስት በቀጣይ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎችን  የሚሰራ ሲሆን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ግን በባንክ ስራ የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሳተፉ የማድረግ ዕቅድ አለመውጣቱን ነው ያብራሩት። ይሁንና አሁን የተጀመሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤት እየታየ የሚቀየር ነገር ይኖራል ብለዋል በምላሻቸው። የፖለቲካ ልዩነታችን አገሪቷን አንድ ከማድረግና የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ሊመልሰን አይገባም ያሉት ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ያሉ ስጋቶችን ለመፍታት ሁላችንም ተረባርበብ ከፊታችን ያለውን ዕድል እንጠቀም  የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ እምብዛም ከጥያቄ ያልዘለሉ አስተያየቶች መሰጠታቸውን ቀጥለዋል። እኔና ባልደረባዬም የምንፈልጋቸው የኢኮኖሚ ምሁራን አስተያየት እየናፈቀን የአስተያየት መስጫ ጊዜው በመጠናቀቁ ቅሬታ ተሰምቶናል። ምሁራኑን የምናገኝበት ቦታ ከዚህ የተሻለ ሊሆን እንደማይችል የነበረን ተስፋ በተስፋ ብቻ ተጠናቋል። የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካው ባለፈ በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ሃላፊነታቸው ቢሆንም ከሙያው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች ሀሳብና አስተያየታቸውን ቢሰጡ “የሚፈለገው ውጤት ይመጣል” የሚል ሀሳብ አለኝ በግሌ። ከዚህ መድረክ የታዘብኩት ዋናው ነገር ግን ችግሮችን ወደ ሌላ መግፋትና ራስን የመፍትሔ አካል አድርጎ አለማየትን ነው። ይህ አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰነድ አሁን ላለውም ሆነ ወደ ፊት ለሚመጣው የመንግስት ስርዓት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ዘላቂና አስተማማኝ የሚሆንበትን ሁኔታ የሚያመላክት እንዲሆን “ይህ ቢጨመር ይህ ቢቀነስ” የሚለው ሀሳብ ነበር ጎልቶ መውጣት ያለበት። የአገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም 'ልማድ' በሚመስል መልኩ አሉታዊ ነገሮችን ብቻ እያጎሉ እሱን ከመንቀፍ ችግሩን ከስሩ መፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ማመላከት ይልመድባችሁ።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም