እየተሻሻለ ያለው ስርዓተ ትምህርት በሙከራ ደረጃ በ2013 ዓ.ም መተግበር እንደሚጀምር ተገለፀ

88
ነሀሴ 29/2011 እየተከለሰ ያለው የኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት በተመረጡ የትምህርት ክፍሎች በ2013 ዓ.ም መተግበር እንደሚጀምር የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። አገር ዓቀፍ የአጠቃላይ ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ማጠቃለያ ጥናት ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ላይ በ2001 ዓ.ም የተሻሻለው ስርዓተ ትምህርትን የዳሰሰ ጥናት ቀርቧል። የዳሰሳ ጥናቱ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ድጋፍ በካምብሪጅ ኢንተርናሽናል አሰስመንት የተካሄደ ነው። በጉባኤው ላይ እንደተገለፀው፤ የአገሪቱን ስርዓተ ትምህርት ለመከለስ በ2011 ዓ.ም የተጀመረው ስራ ትግበራ አምስት አመታትን የሚፈጅ ነው። የሚኒስቴሩ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው እንዳሉት፤ ዩኒሴፍ በአጠቃላይ ለስርዓተ ትምህርቱ ክለሳ የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ ቃል ገብቷል። ጥናቱ በስርዓተ ትምህርቱ ላይ ያሉ ጥንካሬና ድክመቶችን በመለየት ለትምህርት ጥራት አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በዛሬው መድረክ በጥናቱ የተገኙ ውጤትና ምክረ ሃሳቦች ላይ ሙያዊ ትችት እንደሚቀርብበትና ይህም ለስርዓተ ትምህርቱ ክለሳ እንደግብዓት እንደሚወሰድ አስረድተዋል። የስርዓተ ትምህርቱ ስድስት ደረጃዎችን የያዘ ሲሆን የመጀመሪያው ደረጃ የሆነው ጥናት መጠናቀቁንና ሌሎች የስልጠና ማዕቀፎችንና መሰል ስራዎች በ2012 ዓ.ም እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በአምስት አመት ውስጥ ወደሙሉ ትግበራ ይሸጋገራል ተብሎ የሚጠበቀው ስርዓተ ትምህርቱ በ2013 ዓ.ም በተመረጡ የትምህርት ደረጃዎች የተሻሻለው ስርዓተ ትምህርት ሙከራ እንደሚደረግም ተናግረዋል። የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፂዮን ተክሉ በበኩላቸው በጥናቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው አገሮች የስርዓተ ትምህርትና ተሞክሮ ለመዳሰስ መሞከሩን ጠቁመዋል። የደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ህንድ ተሞክሮ መቀመሩን ገልፀው፤ አገር በቀል እውቀት፣ ግብርና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂና መሰል ጉዳዮች በጥናቱ ላይ መዳሰሳቸውን አስረድተዋል። በዛሬው ጉባኤ 'ስለትምህርት ጉዳይ ያገባናል' ያሉ አካላት እንደተሳተፉ ገልፀው፤ በነገው እለትም በስርዓተ ትምህርቱ ዙሪያ 10 አርዕስቶች ተለይተው ቀጣይ አቅጣጫውን ለማመላከት ምክክር እንደሚደረግ አስረድተዋል። በኢትዮያ የዩኒሴፍ ተወካይ አዲል ኮድር ጉባኤው በርካታ አገሮች ስርዓተ ትምህርታቸው 21ኛው ክፍለ ዘመን በሚጠይቀው መልኩ ለመቃኘት በሚሰሩበት ወቅት የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ጠንካራ ስርዓተ ትምህርት ጥራት ላለው ትምህርት መሰረት መሆኑን ገልፀው፤ ተማሪዎችን፣ መምህራን ፖሊሲ አውጪዎችና የትምህርት ማህበረሰቡን የሚያገናኝ መሆኑንም ተናግረዋል። ዩኒሴፍ ለስርዓተ ትምህርቱ ቀረጻ የሚያደርገውን ድጋፍ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም