በጃናሞራ ወረዳ በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ

52
ጎንደር ሰኔ 7/2010 በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደጉ መኳንንት ለኢዜአ እንደተናገሩት  የተፈጥሮ አደጋው የተከሰተው በወረዳው በክልል ቀበሌ ሰንሰለት በተባለው ልዩ ጎጥ ነው፡፡ ከትናት በስቲያ ከረፋዱ 5 ሰአት እስከ 8 ሰአት በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ባልና ሚስትና ሁለት ልጆቻቸው የተጠለሉበት መኖሪያ ቤታቸው በጎርፍ ተወስዶ ህይወታቸው አልፏል፡፡ በተጨማሪም ዝናቡን ለመጠለል በቤቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሁለት ልጆችም ህይወታቸው ማለፉን ዋና ኢንስፔክተር ተናግረዋል፡፡ በመኖሪያ ቤቱ ተጠልለው ህወታቸው ካለፈው ስድስት ሰዎች መካከል የአባወራውና የእማወራው አስከሬን በህብረተሰቡ ትብብርና ፍለጋ ተገኝቶ ስርአተ ቀብራቸው መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ሌሎች የአራት ሰዎች አስከሬን ፍለጋ መቀጠሉን የተናገሩት ኢንስፔክተሩ በጎርፉ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች 2 ሰዎች ደግሞ በመካነ ብርሃን ከተማ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡ የሟቾቹ መኖሪያ ቤት ለጊዜው ግምቱ ካልታወቀ ንብረት ጋር በጎርፍ ተወስዶ ከጥቅም ውጪ መሆኑንም ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡ የጃናሞራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው አዳነ በበኩላቸው በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ በ15 ሄክተር መሬት ላይ የተዘራ የገብስ፣ የስንዴ፣ የባቄላና የድንች ሰብል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ጉዳት ለደረሰባቸው አባወራ አርሶአደሮች ተተኪ ዘርና ማዳበሪያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የወረዳው አስተዳድር ቦታው ድረስ በመሄድ ምልከታ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም