የአጭር ጊዜ የቴክኖሎጂ ስልጠና ያገኙ ወጣት ሴቶች ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን አበረከቱ

96
ነሀሴ 29/2011 በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለአጭር ጊዜ ስልጠና ያገኙ ወጣት ሴቶች ችግር ፈቺ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ መተግበሪያ የፈጠራ ውጤቶችን መስራት ችለዋል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በቴክኖሎጂ ፈጣን ለውጥና ሽግግር ውስጥ በምትገኘው ዓለም በእጅ የሚሰሩና በወረቀት ብዛት ቢሮ የሚያጨናንቁ ተግባራት በዘመናዊና ቀላል ቴክኖሎጂዎች እየተተኩ ነው። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች አይነተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑም መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለመሆኑ ሲነገር ይደመጣል። ሴቶችን ወደኋላና ማጀት ውስጥ ብቻ የሚያስቀሩ አመለካከቶችን ለመሻርና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይበልጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየሰሩ ይገኛሉ። ሴቶችም ይህን አሉታዊ አመለካከት በመሻር በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሀብታዊ፣ በፖለቲካዊና በቴክኖሎጂ ሥራዎች ላይ ከመሳተፍ በዘለለ ባለቤት ሆነው በመስራት ውጤት ሲያስመዘግቡ እየተስተዋለ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከእንጦጦ ፌሎሺፕ ጋር በመተባበር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተውጣጡ 20 ሴቶች የሰጠውን የሶስት ወር የቴክኖሎጂ ስልጠና አጠናቆ ትናንት አስመርቋቸዋል። እነዚህ ሴቶች በወሰዱት ስልጠና የህብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን መስራታቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ መሆን እንደሚችሉ አመላክቷል። የወይንእሸት ኤሊያስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ናት፤ በእንጦጦ ቴክኖሎጂ ፌሎሺፕ  ፕሮግራም ባገኘችው ስልጠና የቴክኖሎጂ ፈጠራ  ውጤት  አበርክታለች። ወጣቷ  ከጓደኞቿ ጋር በመሆን አስጠኚና አጥኚን በቀላሉ ማገናኘት የሚያስችል ሲስተም ሰርታለች፤ ቴክኖሎጂው ለበርካቶች የስራ እድል እንደሚፈጥርና የአጥኚና አስጠኚን ጊዜ እንደሚቆጥብ ገልጻለች። ሌላዋ  የዌብሳይት ዲቨሎፒንግ ሰልጣኝ ወጣት ትዕግስት አሸኔ በጤናው ዘርፍ ላይ ያተኮረ የቴክኖሎጂ ሲስተም ከጓደኞቿ ጋር ሰርታለች። ይህም በሆስፒታሎች ወረቀት ነክ ስራዎችን የሚያስቀርና የሰራተኛ ቁጥር በመቀነስ ሀኪሞች በቴክኖሎጂ ታግዘው  ህሙማንን በለላሉ የሚከታተሉበት ስርዓት መተግበሪያ እንደሆነ ተናግራለች። የኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር እንደገለፁትም እንደ አገር የተያዘውን የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢኖቬሽን በማስፋት ሀብት ፈጠራን ለማምጣት እየተሰራ ነው። በአገራዊ ለውጡ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ምርምር ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች መሆናቸውንና 25 በመቶ ያህሉም ለሴቶች መሰጠቱን ተናግረዋል። የእንጦጦ ቴክኖሎጂ ፌሎሺፕ መስራች የሆነችው ወጣት ወንጌላዊት ተካ በበኩሏ የትምህርት ዕድል አግኝታ ካናዳ ከገባች በኋላ የአገሯን ልጆች ለማገዝ ከኢኖቬሽን ሚኒስትር ጋር ፕሮግራሙን ማዘጋጀቷን ገልፃለች። ስልጠናውን ለመስጠት ሴቶች ላይ ትኩረት የተደረገበትን ምክንያትም አብራርታለች። በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር አንቶኒ ቼቫሪየር ፕሮጀክቱ ወጣት ሴቶች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ እንዲያበለጽጉ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል። ካናዳ የኢትዮጵያ የልማት አጋር እንደ መሆኗ ሴቶችን በቴክኖሎጂ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም