የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማስፋት ዓለም አቀፍ ጥረት ያስፈልጋል

80
ነሐሴ 29 /2011 የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነትን ለማስፋት ዓለም አቀፍ ጥረት እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት አመለከተ። የተባበሩት መንግስታት የንግድ ልማት ጉባዔ የ2019ን የዓለም የዲጂታል ምጣኔ ሃብት ሪፖርት ዛሬ በአዲስ አበባ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ በዓለም ዲጂታል ምጣኔ ሃብት ፍሰት፣ መረጃና ፈንድ ላይ ያተኮረው ጥናት ውጤት ነው። ለዲጂታል መረጃና ስርዓት ሪፖርቱ የተለየ ትኩረት በመስጠት በዲጂታል ምጣኔ ሃብት በዋናነት እሴት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሲል አስቀምጧል። ሪፖርቱ ዲጂታል ምጣኔ ሃብት ዓለም ከተገናኘበትና በኤሌክትሮኒክስ ግብይት እየተጠቀመበት ካለው በተሻለ ሊያስገኝ የሚችለውን አቅምና ዋናዋና የልማት አማራጮችም አመላክቷል። እንደ ሪፖርቱ ምልከታ በዘርፉ ሃብት በማፍራት በኩል አሜሪካና ቻይና ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ አፍሪካና ላቲን አሜሪካ ወደኋላ ቀርተዋል። ቻይናና አሜሪካ በኢንተርኔት የሚፈጸሙ የዓለም 50 በመቶ ክንውኖችን ድርሻ ይወስዳሉ። ፈጣን የገንዘብ ዝውውር ማድረግ የሚያስችሉ 75 በመቶ ቴክኖሎጂዎች የሚገኙት በእነዚሁ አገራት መሆኑንም ሪፖርቱ ገልጿል። ይህ ልዩነት በአገራት መካከል በዲጂታል ምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ላይ ኢ-ፍትሃዊነት እንዳይፈጥር ከወዲሁ ትኩረት እንደሚያሻው ነው የተጠቆመው። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ ንግድ ፖሊሲ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ዴቪድ ሉኪ ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ ለታዳጊ አገሮች የራሱ ዕድልና ተግዳሮት አለው ብለዋል። የአፍሪካ አገራትም ዲጂታል ምጣኔ ሃብት ያመጣቸውን ዕድሎች መጠቀም በሚያስችል ቁመና ላይ መራመድ እንዳለባቸው መክረዋል። ኢትዮጵያ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር በማቋቋም እያከናወነችው ያለው ተግባር መልካም ጅማሮ መሆኑን በመግለጽ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካሪ ዶክተር ታፈረ ተስፋቸው በበኩላቸው አገሪቱ በዲጂታል ምጣኔ ሃብት ስትራቴጂ በማውጣት ሽግግር ያደርጋሉ ከሚባሉ የአፍሪካ አገራት አንዷ ነች ብለዋል። ለዚህም የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር አዲስ ፖሊሲ እያወጣ እንደሆነና ኮሚሽኑም በአይሲቲ ፓርክ ባለሃብቶች መሳብ የቻልበትን ሁኔታ እያጠና መሆኑን አክለዋል። እንደ አማካሪው ገለጻ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምህንድስናና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎችና የህዝብ ብዛቷ ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት መልካም ዕድሎች መካከል ናቸው። ይህን ዕድል ለመጠቀም በዓለም ላይ በዲጂታል ምጣኔ ሃብት የታወቁ ኩባንያዎች ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ፍጥነትን በማሻሻልና የሌሎች ዘርፎች ተግዳሮቶችን በመፍታት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በአፍሪካ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትስስር አንዷ ለመሆን እየሰራች ነውም ብለዋል። ዲጂታል ኢኮኖሚ የንግድና ልውውጦችና ሙያዊ ግንኙነቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካኝነት በማከናወን ዓለምን የሚያስተሳስርና ስራን የሚያቀላጥፍ አሰራር ነው።                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም