ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ በትኩረት ይሰራል

63
ነህሴ 29 / 2011  (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ አንድ በመቶ ለማውረድና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ። በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባና የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ በወልዲያ ከተማ ውይይት ተካሄዷል። የመምሪያው ሃላፊ አቶ ሸጋው አገሸን በውይይቱ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በዞኑ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት ቢከናወኑም በቅንጅት መጓደል ምክንያት ማሳካት አልተቻለም። ባለፈው ዓመት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ከሁለት በመቶ በታች ለማውረድ ቢታቀድም 13 ሺህ 300 ተማሪዎች ትምህርታቸውን በማቋረጥ ከታቀደው በላይ አምስት ከመቶ መድረሱን ገልፀዋል። በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ ለማሳያነትም በሀብሩ ወረዳ አረሪት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ቁጥር በእጅጉ በመቀነሱ ባለፈው ዓመትና በዚህ ዓመት ለብሄራዊ ፈተና 26 ተማሪዎች ብቻ መቀመጣቸውንና ትምህርት ቤቱ የመዘጋት አደጋ እንደተጋረጠበት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአዲሱ የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በማሻሻል፣ ሳቢና ማራኪ በማድረግ፣ ተማሪዎችን ተከታትሎ በመመዝገብ በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም በየደረጃውያለው አመራር በባለቤትነት መስራት እንዳለበት አመልክተው፤ በዚህም የአቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር አሁን ካለበት አምስት ከመቶ ወደ አንድ ከመቶ ማውረድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን የእለት ከእለት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከመምህራንና ርዕሳነ መምህራን ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልም በልዩ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል። የራቆቦ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንገሻ በላይ በበኩለቸው ባለፈው ዓመት የተደራጀ የትምህርት ንቅናቄ ባለመከናወኑ የትምህርት ሽፋኑ 80 ከመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዓመት ግን ካለፈው ዓመት ችግር በመማርበወረዳ፣ በቀበሌና በመንደር ደረጃ የትምህርት ንቅናቄ በማከናወንና የቅድመ ምዝገባ ልየታ በማድረግ የተሻለ የትምህር አፈጻጸም ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን በበኩላቸው በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋለው ችግር በየደረጃው ያለው አመራር የክትትል ድክመት ዋነኛ ማሳያ ነው። በዚህ የትምህርት ዘመን የተለዩ ችግሮች እንዲፈቱ ጠንካራ አመራር መስጠትና ማስተካከል ለነገ የማይባል አንገብጋቢ አጀንዳ ነው ብለዋል። በዞኑ በ2012 የትምህርት ዘመን 51 ሺህ አዲስ እና334 ሺ ነባር የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። በወልዲያ ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው የትምህርት ንቅናቄ መድረከ በየደረጃው ያለው አመራር ተሳታፊ ሆኗል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም