በይቅርታ የመሸጋገሪያዋ ንዑስ ወር…

132

ምህረት አንዱአለም/ኢዜአ/

ኢትዮጵያውያን በተፈጥሯዊ የጊዜ ኡደት አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ሊቀበሉ ጥቂት ቀናት ቀርተዋል። ኢትዮጵያ የራሷን የአቆጣጠር ስልት የምትከተል ሲሆን የ13 ወር ጸጋ ባለቤትም ናት። 13ኛዋ ወር ከሌሎቹ 12 ወራት በጊዜ ምጣኔዋ አነስተኛዋ ናት። የጳጉሜ ወር። በወሯ ውስጥ ለተከታታይ ሦስት ዓመት አምስት ቀናት የሚቆጠሩ ሲሆን በየአራት ዓመቱ ደግሞ ስድስት ቀናት ትሆናለች።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፤ ጳጉሜ የዓመቱ “ንዑስ ወር” ነው የምትባለው። በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ለየት ያለችና ከሌሎቹ ባለ 30 ቀ 12 ወራት የተለየችና ጥቂት ቀናትን የያዘች ናት ብለውናል።

ጳጉሜ ከዓመት ወደ ዓመት መሸጋገሪያ ወር ናት፤ በዚህም ምክንያት ከሃይማኖታዊ ተግባራት ባሻገር ማህበራዊ ክዋኔዎች ይፈጸማሉ። አዲስ ዓመት ሲመጣ መልካም ያልሆነን ነገር በመተው፤ መልካም ነገርን በማሻገር በአዲስ መንፈስ ለመቀበል በጳጉሜ ወር ቀናት ዝግጅት ይደረጋል።

ለአብነትም ሰዎች አዲሱን ዓመት በበቀልና በጥል እንዳይቀበሉት በጳጉሜ ወር ተምሳሌታዊ ክዋኔዎች ይፈጸማሉ። በገጠሩ አካባቢ ሽማግሌዎች የተጣሉ ሰዎችን ቀርቦ በማስታረቅ የተቀያየሙት ቅያሜን እንዲሽሩ ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች አዲሱን ዓመት የአንድነት ይሁን ብለው መርቀው የተጣላን አስታርቀው ትውልዱን የሚያስተምሩበት ወቅት እንደሆነም ይነገራል።

የአካላቸውንና የህሊናቸውን ጉድፍ በማጽዳት ለአዲስ መልካም ነገር ራሳቸውን ለማዘጋጀትና ለመቀበል፣ ከመንፈስ መታወክም ለመፈወስ፤ በጳጉሜ ወር የገጠር ሰዎች ወንዝ ወርደው ይታጠባሉ። በጳጉሜ ወር ወንዝ ወርዶ መታጠብ እርቅን፣ ሰላምንና ፍቅርን  መቀበል፣ ቂምን በደልን ማራቅ ተደርጎም ይወሰዳል፤ ተምሳሌቱ።

በዚህች ወር መጨረሻ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዕለትም “የፀብና የክፉ መንፈስ ውጣ በጎ መንፈስ ግባ” ተብሎ በተምሳሌትነት የብርሃን የተስፋ የፍቅር ተምሳሌት የሆነው ችቦ በጋራ እንደሚለኮስ ነው መምህር ዳንኤል የገለጹት።

በአዲስ ዓመት በቀልን ረስቶ በይቅርታ ፍቅርን ለመላበስ ሲታሰብ…

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እንደሚሉት፤ ይቅርታ ሰዎች የደረሰባቸውን ግፍና በደል እያሰቡ ለቀጣይ ሌላ ጉዳትን እንዳያመጡ እና በክፋት የተፈጸመባቸውን ተግባር  እንዳይፈጽሙት ማለፍ ነው።

ሰዎች ይቅርታ የሚያደርጉት ለራሳቸው፣ ለማህበረሰባቸው፣ እና ለሀገራቸው ሲሉ ነው። ሰው በደልን በይቅርታ ካለፈ በተሻለ ሰላምና ነጻነት ይኖራል፤  ውስጣችን ላይ ሁል ጊዜ ቂምንና በቀልን ይዘን ከተቀመጥን ህመምተኛ ሆነን የምናልፍበት እድል ሰፊ ይሆናል ነው ያሉት ኡስታዝ።

ሀኪምና የስነመለኮት እውቀት እንዳላቸው የነገሩን ዶክተር ወዳጄነህ መኃረነ “በቀል ሰው ያደረገብህን ክፉ ነገር መልሰህ በሌላ ክፉ ነገር መክፈል ማለት ነው፤ ያ ልክ እንዳደረገብኝ አደርግበታለሁ እንደጎዳኝ እጎዳዋለሁ ብለህ የምታደርገው ጥሩ ያልሆነ ነገር ነው፤ ይቅርታ ደግሞ ሪሊዝ ማድረግ ነው፤ የተደረገብህን ነገር ትተህ ማለፍ ነው” ይላሉ።

ይቅርታ ከሚደረግለት ሰው የበለጠ ይቅርታ አድራጊው ይጠቀማ ያሉት ዶክተር ወዳጄነህ፤ ሰው በውስጡ ቂም፣ ጥላቻ ሲያስቀምጥ አዕምሮው ይታወካል፤ ሰላም አያገኝም፤ ደስተኛ አይሆንም፤ ወደፊት መሄድ አይችልም ብለዋል።

“ሁልጊዜ የምታስታውሰው ያንን የተደረገብህን በደል ከሆነ ሰላም የምታጣው አንተ ነህ፤ የበደለህን ሰው ይቅርታ ስታደርግለት ግን የአዕምሮህ ሰላም ይመለሳል፤ ደስተኛ ትሆናለህ።” ሲሉም ስለ ይቅርታ ፋይዳ ይገልጻሉ።

“በነገራችን ላይ እኔ ሀኪምም ነኝ፤ ይቅርታ አለማለት በህክምና አልሰር ለተባለ የጨጓራ በሽታ ይዳርጋል፤ አንዳንድ በካንሰር ላይ የሚደረጉ ጥናቶች ይቅር አለማለትና ቂም ተፅዕኖ እንዳላቸው ያነሳሉ “  በማለትም ነው ዶክተር ወዳጄነህ የጠቀሱት።

ኡስታዝ አቡበከር ኢትዮጵያ ወደፊት የምትሻገርበት አንዱ መንገድ ይቅርታ መሆኑን ያነሳሉ።

“በዚህች ሀገር ላይ በትናንት ታሪኮቻችን በጣም ተጎዳድተናል። ተገፋፍተናል። አንዱ ለአንዱ አደጋ ሆኖ፤ ስጋት ሆኖ አንዱ አንዱ ላይ ጭካኔን ፈፅሞ ስቃይን አድርሶ አልፏል። ይቺ ሀገር እንድትቀጥል፤ የተሻለ ሀገር ሆና እንድትኖር ስናስብ ግን ይህን ሀሳብ ማውጣት ነው ያለብን። ይቅርታን ከልባችን አውጥተን ያለፉ በደሎችን ረስተን የትናንትን እኛ ያልነበርንበትን ታሪክ እንደሆነ አስበን ነገን የተሻለ አድርገን ለመኖር ስንሰራ ብቻ ነው ይችን ሀገር የምናሻግራት፤ የተሻለ የተረጋጋ የሰላም ሀገር የምናደርጋት” ሲሉም ይመክራሉ።

ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሰዎች የእምነት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ምሁራንና በህይወታቸው በደል የደረሰባቸው ሰዎችና በክፋት የተጎዱ ሰዎች ከፊት በመውጣት የይቅርታ ምሳሌ መሆን እንዳለባቸውም ራሳቸውን ምሳሌ በማድረግ ነው ያቀረቡት።

“እኔ ትላንትና ተገርፌያለሁ፤ ታስሬያለሁ በዚህ ስርዓት ተንገላትቻለሁ፤ ግን እነዚያ እኔን የገረፉኝ፣ ያሰቃዩኝ፣ ያንገላቱኝን ሰዎች ይቺ ሀገር እንደ ሀገር እንድትኖር ስለማስብ እኔ ያንን ነገር መርሳት አለብኝ ብዬ አስባለሁ። ይቅር ብያለሁ፤ እኔ በእነዚያ ሰዎች መታሰር የምጠቀመው ጥቅም፣ በመሰቃየታቸው የማገኘው መልካም ነገር አለ ብየ አላስብም። ይቅር በማለት ብቻ ነው የጠፉትን ነገሮች ልናቆማቸው ይምንችለው። በተለይ ተበድለው ያለፉ የተገፉ ሰዎች ከፊት መውጣት አለባቸው።”ብለዋል

ይቅርታ ለማድረግ፤ ፍቅርን በተግባር ለማሳየት ከልብ የሆነ ፈቃደኝነት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዶክተር ወዳጄነህ፤ በዓለም አስከፊ ከሚባሉ የሰው ልጅ ጭፍጨፋ የተከሰተባት ሩዋንዳ የተደረገው የይቅርታ ታሪኮችንም በማንሳት ሰው እንዴት በደልን ትቶ ይቅርታን እንደሚያስበልጥ አጫውተውናል።

“ሩዋንዳ ውስጥ አምስት ልጆቿን የገደለባትን ሰው ፊትለፊት አግኝታ ይቅር ብላዋለች፤ እጇን የቆረጠባትንና አንድ ልጇን የገደለባትን ሰው ታስሮ ሲወጣ አግኝታው ይቅርታ አድርጌልሃለሁ ያለች ሴት መኖሯንም ሰምተናል፤ ከፍተኛ የይቅርታ አቅም ያላቸው ሰዎች አሉ። እነሱ ያንን ሰው ይቅር ማለት ከቻሉ በቀልን ጥሎ መሻገር እኮ ነው።”በማለትም የይቅርታን ጠቀሜታ ይገልጻሉ።

የዘመን ሽግግር ዋዜማ ላይ ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለማህብረሰብ እና ለሀገር የሚጠቅም አዲስ ነገር ማቀድ መጀመር አለብን የሚሉት ኡስታስ አቡበከር፤ “አንድ የተሻለ ነገር ለመፍጠር ንጹህ ሆኖ መውጣት ያስፈልጋል፤ ስለዚህ አዲሱን ዓመት ስንቀበል በንጹህ ልብ በይቅርታ ያለፈውን ረስተን መሆን አለበት” ነው ያሉት።

አዲስ ዓመት ሲመጣ ያለፈውን ለመተው፤ ወደ አዲስ ነገር ለመግባት አጋጣሚውን ይሰጣል ያሉት ዶክተር ወዳጄነህ፤ ያለፈውን ምዕራፍ እንዳለ ዘግቶ ወደ አዲስ በጎ ምዕራፍ ለመሻገር ጳጉሜ የመሸጋገሪያ እድል ናት ብለዋል።

“ይቅር ያለማለትና የጥላቻ የቂም ኮተት ይዤ አልገባም፤ ወደ አዲስ ዓመት ስሸጋገር አራግፌ ትቼው ነው መሻገር ያለብኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ የድሮ ትርክት እያመጡ እከሌ ንጉሥ እንዲህ አድርጎ፤ ይህኛው ብሔር በዚህኛው ላይ እንዲህ አድርጎ ብለን ጊዜ ከምንወስድ መተውና ይቅር መባባል፤ ያለፈውን ረስተን ለወደፊት ሰላማችን ጥሩ የምንሰራበት ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አምናለሁ።” ሲሉም ነው የገለጹት።

መምህር ዳንኤል በበኩላቸው በጳጉሜ ወር እርቅን ፈፅሞ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ብርታት እና አስተዋይነት ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።

“ብጥብጥና ጸብ እንደማይጠቅም ማንም ሰው ያውቀዋል፤ ሆኖም ፍቅርን ለማስተማር፣ አብሮ መኖርን ለማሳየት፤ በደል በድጋሜ እንደማይፈፀም ዋስትናንውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባም ተናግረዋል።

“ጳጉሜ መሸጋገሪያችን እንደመሆኗ ጸፀቡን አርቀን፣ ጥልንና በደልን ሽረን፣ ፍቅርንና ይቅርታን መላበስ አለብን። በኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ብዙ ጉዳት ደርሷል። አሁንም ብዙ ጉዳቶች ሲፈፀሙ እያየን ነው። ስለዚህ በጳጉሜ ወርም እንደ ሀገር እንደ ህዝብ የንፅህና፣ የፍቅርና የአብሮ መኖርን ፋይዳ በተግባር ለማሳየት ከልብ መዘጋጀት አለብን።” ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።