በኢትዮጵያ እግር ኳስ የእድሜ ተገቢነት ችግር ሊፈታ ያልቻለ ችግር ሆኖ ቀጥሏል

72
ነሀሴ 26/2011 በኢትዮጵያ እግር ኳስ የእድሜ ተገቢነት ችግርና የታዳጊዎች ምልመላ ሊፈታ ያልቻለ ችግር ሆኖ መቀጠሉ ተገልጿል። ችግሩን ለመፍታት በሃላፊነት መስራትና እድሜ መለያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ያስፈልጋል ተብሏል። ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ቡሩንዲ ባስተናገደችው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ምክር ቤት (ሴካፋ) ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ በሶስት ተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነት ችግር የተነሳ ለቅጣት መዳረጓ ይታወሳል። በዚህ ቅጣት ከሶማሊያ ጋር ኢትዮጵያ ባደረገችው ጨዋታ 3 ለ 1 ብትረታም በፎርፌ ያገኘችው ድል ለሶማሊያ ተሰጥቷል። ይህ ብቻ አይደለም በእድሜ ተገቢነት የተቀጡት ተጫዋቾች ከውድድሩ እንዲሰናበቱ፣ ቡሩንዲ በነበራቸው ቆይታ የወጣባቸውን የአምስት ሺህ ዶላር ወጪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሸፍንና በተጫዋቾቹ ምትክ ሌሎችን እንዳይተካ መደረጉ ይታወሳል። ይህ ችግር በዓለም ዓቀፍ ውድድር ብቻ የሚታይ ሳይሆን በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ፈተና ሆኖ ለእግር ኳሱ እድገት እንቅፋት ሆኗል። ብዙዎቹ ክልሎች ለውድድር የሚልኳቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነት ችግር ይነሳባቸዋል። መነሳት ብቻ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ መሆን ከነችግሩ ለመጓዝ አስገድዷል። በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለታዳጊዎችና ለተተኪዎች እድል የማይሰጥበትና የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ የጎላ ችግር እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። 'ኮፓ ኮካ ኮላ' ዓይነት የታዳጊዎች ውድድር ሲካሄድ በርካታ ወደብሔራዊ ቡድን እንደሚያድጉ የሚገመቱ ተጫዋቾች ከመንገድ መቅረታቸው አንዱ መንስኤ ታዳጊዎችን በአግባቡ እንዲተካኩ ባለመደረጉ እንደሆነም ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኩሩ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እድሜያቸው ትንሽ የሆኑና ለእግር ኳሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉና ተስፋን የሚጭሩ ታዳጊዎች በርካቶች ናቸው። በእድሜ ትንሽ የሆኑና ከፍተኛ የኳስ ክህሎት ያላቸው ታዳጊዎች ቢኖሩም ለውድድር የሚቀርቡት የእድሜ ተገቢነቱን የሚጥሱት እንደሆኑ ገልጸዋል። በተለይም ክልሎች ተጫዋቾችን የሚመለምሉበት መንገድ የዕድሜ ተገቢነት ችግር ያለበት መሆኑን አስረድተዋል። የእድሜ ተገቢነትን ችግር ለመፍታት አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎችና የክልል ፌዴሬሽኖች በቂ እገዛ እያደረጉ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ለውድድር የሚለዩ ታዳጊ ተጫዋቾች ዕድሜ ልየታ የሚካሄደው ኤምአርአይ በመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ታግዞ ሳይሆን በግምት በመሆኑ ችግሩን መፍታት አዳጋች መሆኑንም አቶ ተናግረዋል። ''የእድሜ ችግርን ለመቅረፍና እግር ኳሱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በስፖርቱ ልማት ላይ በስፋት መስራትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ያስፈልጋል'' ብለዋል። እንዲሁም በስፖርቱ ላይ ያሉ ሁሉም አካላት ዋንጫ ማግኘትን ብቻ አላማ ማድረግ ሳይሆን እግር ኳሱንም ታዳጊዎቹንም ሊጠቅም በሚችል መልኩ በሃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም