በአማራ ክልል 17 ሚሊዮን የሚጠጋ የቡናና የፍራፍሬ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጀ

70
ባህር ዳር ሰኔ 7/2010 በአማራ ክልል በተያዘው ክረምት የሚተከል 17 ሚሊዮን የሚጠጋ የቡናና የፍራፍሬ ችግኝ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ግርማ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኙ የተዘጋጀው በ6 ሺህ 700  የመንግስት፣ የግል፣ የፕሮጀክትና የማህበራት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ነው። ከተዘጋጀው ችግኝ ውስጥ 10 ሚሊዮን 390 ሺህ የሚሆነው በሽታን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ችግኝ መሆኑን ተናግረዋል። ቀሪው የማንጎ፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ የአፕልና የብርቱካን ችግኝ ነው፡፡ ችግኙ ለልማቱ ተስማሚ ናቸው ተብለው በክላስተር በተለዩ 20 ወረዳዎች በሚገኝ 14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከተያዘው ወር መጨረሻ ጀምሮ እንደሚተከል ጠቁመዋል። እንደ  አቶ ግርማ ገለፃ ለችግኝ መትከያ  እስካሁን ከ613 ሺህ በላይ  ጉድጓድ በአርሶ አደሮቹ ተቆፍሯል። የቡናና ፍራፍሬ ችግኙ ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገለት ከሶስት ዓመት ጀምሮ ምርት መስጠት እንደሚጀምር አስረድተዋል። በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የሮቢት ባታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረፃድቅ አሻግሬ በሰጡት አስተያየት በዚህ ዓመት 200 የማንጎ ችግኝ ለመትከል ጉድጓድ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከአምስት ዓመት በፊት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከተከሉት  የማንጎና አቦካዶ ተክል በዓመት እስከ 15 ሺህ ብር ገቢ  እያገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዘንድሮው ክረምት  250 የተሻሻለ የቡና፣ አቦካዶና ማንጎ ችግኝ ተክለው ለማልማት እየተዘጋጁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የሰባታሚት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደረሰ ሙጬ ናቸው። ቀደም ሲል ቡናን ጨምሮ የአቦካዶና ማንጎ ችግኝ ተክለው እየተንከባከቡ ሲሆን ከቡናው ለፍጆታ የሚሆን ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከሉ ከ14 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች ውስጥ 92 በመቶ መፅደቁ ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም