ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የፈጠሩት አለመረጋጋት በስራችን ላይ ጫና አሳድሮ ቆይቷል…የደቡብ ክልል ም/ቤት

71
ነሀሴ 25/2011 በደቡብ ክልል ከሚታየው ፖለቲካዊ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው አለመረጋጋት በክልሉ ምክር ቤት ተግባራት ላይ ጫና ማሳደሩን የምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ገለጹ። ምክር ቤቱ 5ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሃዋሳ እያካሔደ ነው። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የምክር ቤቱ  አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሔለን ደበበ እንደተናገሩት በተለያየ ሁኔታ በክልሉ እየታዩ ያሉት የፖለቲካ ጥያቄዎች በምክር ቤቱ ተግባር ላይ ጫና ፈጥሯል። በምክር ቤቱ ውስጥ በተደራጁ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት የአስፈፃሚዎች አፈፃፀም በየሩብ ዓመቱ እየተገመገመና ግብረ መልስ እየተሰጠው ቢቀጥልም ካለው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ የተነሳ የምክር ቤቱ የ2011 ግማሽ ዓመት ጉባኤ ሳይካሄድ መቅረቱን ተናግረዋል። ይህም ሊሆን የቻለው የመንግስት ዋንኛ ተልዕኮ ለሆነው ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱንና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ተግባር ቅድሚያ በመሰጠቱ እንደሆነም ጠቁመዋል። ሀገራዊ ለውጥ ከችግር በፀዳ መልኩ ሊከናወን እንደማይችል የገለፁት አፈ-ጉባኤዋ “በትጋትና በታታሪነት በመሰለፍ እንዲሁም ነገን አርቀው የሚያዩ ኃይሎችን በማብዛትና ሕብረትን በመጎናፀፍ በዚህ የለውጥ ምዕራፍ ላይ የሚገጥሙንን መሰናክሎች መሻገሪያ መሰላል በማድረግ ልንረባረብ ይገባል” ብለዋል። ይህንን ምዕራፍ ለማለፍና የዜጎች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በስሜት ከመሔድ ይልቅ ከችግሮች በላይ ከፍ ብሎ በማየት የህዝቦችን ዘላቂ ጥቅምና ሠላም በሚያረጋግጡ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ ከምክር ቤቱ አባላት የሚጠበቅ ቁልፍ ሚና እንደሆነም አስረድተዋል። አሁን ያለውን አንፃራዊ ሰላም ከማጠናከር ባለፈ የኑሮ ውድነት ፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት እና የምርት መቀነስ በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ የክልሉ ወቅታዊ ፈተናዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል። አፈ-ጉባኤዋ አክለውም አሁን ላይ ትልቁ ፈተና እየሆነ የመጣውን ስርዓት አልበኝነት በመፀየፍ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት የሚደመጡበትን ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር የምክር ቤቱ አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸውም ብለዋል ፡፡ ምክር ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉባኤ በመጥራት የ2011 በጀት ዓመት ሪፖርትን እንዲሁም የ2012 ዕቅድን እንደሚገመግምም አፈ-ጉባኤዋ ጠቁመዋል። ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባኤ አጀንዳዎቹ የ8ኛ መደበኛ ጉባኤውን አጀንዳ ተወያይቶ ማፅደቅ እንዲሁም የ2012 ረቂቅ በጀት አዋጅና የተለያዩ ሹመቶችን ማጽደቅ እንደሆነም ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም