መንግስት በኦሮሚያ የቤተ-ክህነት ጽህፈት ቤት ለማቋቋም የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን በአፋጣኝ እንዲያስቆም ጥሪ ቀረበ

151
አዲስ አበባ ኢዜአ 24/2011 መንግስት በኦሮሚያ ክልል ራሱን የቻለ ቤተ-ክህነት ጽህፈት ቤት ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመሩ አካላት ከተግባራቸው በአፋጣኝ እንዲታቀቡ ያደርግ ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀረበች። የቤተ-ክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ ጉዳዩን አስመልክቱ ዛሬ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። ሰሞኑን በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን መሪነት በኦሮሚያ የቤተ-ክህነት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የማቋቋም  ዝግጅት  ተጀምሯል። በጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ጠቅላይ ስራ አስኪያጅ ርዕሰ ደብር መሃሪ ሃይሉ የተነበበው የሲኖዱሱ  መግለጫ እንደሚለው ግን  ይህ ተግባር ከቤተክርስቲያኗ መዋቅር ውጪ ነው። ለረጅም ዓመታት ለሁለት ተከፍሎ የቆየው የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ ባለፈው አንድ ዓመት ወደ አንድ መጥቶ በሰላም እየሰራ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል። ተከታዮቿን ስለሰላምና አንድነት እየሰበከች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ ከቤተክርስቲያኗ ዕውቅና ውጪ በኦሮሚያ ክልል ቤተ-ክህነት ጽህፈት ቤት ለማቋቋም የተጀመረው እንቅስቃሴ ህገ-ወጥ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል። "ቤተ-ክርስቲያኗ ህጋዊ እውቅ ያላት በዘፈቀደ የምትሸራረፍ አይደለችም" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ስራ አስኪያጁ "ጥያቄውን ማቅረብ መብት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ጥያቄው መቅረብ ያለበት በህጋዊ ስርዓት ነው፤" ብለዋል። አለበለዚያ በቤተ-ክርስያኒቱ ላይ የመከፋፈል አደጋን ያስከትላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል። በመሆኑን ይህ ሀሳብ ከቤተ-ክርስቲያኗ መዋቅር ውጪ በመሆኑ መንግስት እንዲያስቆመው ጥሪ አቅርበዋል። በመግለጫው ላይ የተገኙት የቤተክርስቲያኗ የተለያየ መምሪያ ሃላፊዎችም እንቅስቃሴው ተገቢ አለመሆኑን አብራርተዋል። በክልሉ ስብከተ ወንጌልንም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ከመቼውም ጊዜ በላይ መልካም ስራዎች እየተሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ቋንቋን መሰረት ያደረገ መከፋፈል ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የሚወገዝ ተግባር ነውም ብለዋል። ሃይማኖት ቋንቋና ድንበር የማይወስነው እንደመሆኑ ቤተ-ክርስቲያኗ በአገሪቷ ትምህርት ሚኒስቴር ባልተቋቋመበት ጊዜ ጭምር ሁሉንም ዜጎች በእኩል ደረጃ የአብነት ትምህርት ትሰጥ እንደነበር በማስታወስ። ሲኖዶሱ ዜጎች በቋንቋቸው ፈጣሪያቸውን እንዲያመሰግኑና እንዲያመልኩ ሰፊ ዕድል እያመቻቸ ባለበት በዚህ ጊዜ እየቀረበ ያለው ጥያቄ አገልግሎትን በቋንቋ ከማስፋት ባለፈ ሌላ ተልዕኮ ያለው መሆኑን የቤተክርስቲያኗ የስራ ሃላፊዎች ያነሳሉ፡፡ ጽህፈት ቤቱን ለማቋቋም እንቅስቃሴውን እየመሩ ነው የተባሉት ቀሲስ በላይ ቀደም ባሉት ጊዜያት በቤተክርስቲያኗ በምክትል ጠቅላይ ስራ አስኪያጅነት፣ በአዲስ አበባ አገረ-ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅነት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት የህግ አገልግሎት መምሪያ ሃለፊ ሆነው አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም