ድርጅቱ በአምቦ ከተማ ለ1ሺህ 728 ችግረኛ ሴቶች ድጋፍ አደረገ

59
አምቦ ኢዜአ ነሐሴ 24/2011፡- ስታንድ ፎር ቫልነረብል የተባለው ድርጅት አምቦ ከተማ ለሚገኙ 1ሺህ 728 ችግረኛ ሴቶች ዱቄትና የምግብ ዘይት ድጋፍ አደረገ። ድርጅቱ ዛሬ ድጋፉን ያደረገው ከአሜሪካ መንግስት ያገኘውን ከ276ሺህ650 ብር በላይ ወጪ በማድረግ ነው። በዚሁ ገንዘብ የተገዙ 126 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና 290 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ መደረጉን የከተማው አስተዳደር ሴቶችና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች አለማየሁ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ድርጅቱ ለችግር የተጋለጡ ህጻናትንና ሴቶችን ለመርዳትና ለማስተማር በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመመገብ፣ የመኝታ የልብስና የትምህርት ቁሳቁሶችን በማማላት እያስተማራቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ቀነአ በበኩላቸው ለተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የምግብ ዘይትና ዱቄት ከተሰጣቸው መካከል ወይዘሮ ጠጅቱ ፈዬራ እና ወይዘሮ ባዩሽ መገርሳ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ወራትም ለ132 ችግረኛ ሴቶች አምስት ወፍጮዎችን በአንድ ሚሊዮን 800ሺህ ብር በሆነ ወጪ አመቻችቶ ተጠቃሚ ማድረጉም ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም