21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ በሩሲያ በይፋ ይጀመራል

96
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 በሩሲያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 21ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ ሩሲያና ሳውዲ ዓረቢያ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀምራል። እ.አ.አ በ2014 በብራዚል በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ማሪዮ ጎትዜ በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠረው ግብ ጀርመን አርጀንቲናን አሸንፋ ሻምፒዮን ከሆነች ዛሬን ጨምሮ 1 ሺህ 432 ቀናት ተቆጥረዋል። የዘንድሮው ውድድር 81 ሺህ ደጋፊዎችን በሚያስተናግደው በሞስኮው ሉዚኒስኪ ስታዲየም ዛሬ ሩሲያና ሳዑዲ ዓረቢያ በሚያደርጉት ጨዋታ በይፋ ይጀመራል። የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ 'የእግር ኳስ ፌስቲቫል' የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። ሩሲያ የዓለም ዋንጫውን ለማስተናገድ ዝግጅቷን ስታደርግ የቆየች ሲሆን አገሪቷ በአጠቃላይ ለውድድሩ ዝግጅት ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች። ለውድድሩ በ11 የሩሲያ ከተሞች 12 ስታዲየሞች 113 የመለማመጃ ስፍራዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ 20 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡትን ዜጎች የሚያስተናግዱ ይሆናል። የመክፈቻ ጨዋታው ከመካሄዱ በፊት ተዋቂ ዘፋኞች ስራቸውን ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል። አሜሪካዊው ፒትቡል፣ ኮሎምቢያዊቷ ሻኪራ፣ አሜሪካዊቷ ጄኔፈር ሎፔዝ፣ ፖርቶሪካዊው ሉዊስ ፎንሲ፣ እንግሊዛዊው ሮቢ ዊሊያምስና ሩሲያዊቷ አይዳ ጋሪፉሊና የመክፈቻ ስነ ስርዓቱን ድምቀት ይሰጡታል ተብሏል። 500 የሚጠጉ ዳንሰኞች፣ የሰርከስ ባለሙያዎችና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ከዘፋኞቹ በተጨማሪ ትርኢት የሚያቀርቡ ይሆናል። የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ይፋዊ መዝሙር የሆነው "ሊቭ ኢት አፕ" ኒኪ ጀምስ፣ ዊል ስሚዝና ኢራ ኢስትሬፊ ለተመልካቾች ያቀርባሉ። ዛሬ በሩሲያና ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የሚደረገውን የመክፈቻ ጨዋታ የ42 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ኔስቶር ፒታና በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እ.አ.አ በ1993 ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ሳዑዲ ዓረቢያ ሩሲያን አራት ለሁለት ማሸነፏ የሚታወስ ነው። በዓለም ዋንጫ ታሪክ አዘጋጅ አገር በመክፈቻ ጨዋታ ተሸንፎ አያውቅም። በስታኒስላቭ ቼርቼሶቭ የሚሰለጥነው የሩሲያ ብሔራዊ ቡድን የመክፈቻ ጨዋታውን ማሸነፍ በደጋፊው ዘንድ ያለውን ጫና በተወሰነ መልኩ የሚቀንስለት ይሆናል። በአንፃሩ በአርጀንቲናዊው ጁዋን አንቶኒዮ ፒዚ የሚሰለጥነው የሳዑዲ ዓረቢያ ቡድን ከምድቡ ለማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማሸነፍ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ይታያል። በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን፣ የቦሊቪያ ፕሬዚዳንት ኢቮ ሞራሌስ፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፓል ካጋሜና የሌሎች አገራት መሪዎችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አብዱራሂምና የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴም በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ ይታደማሉ። እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ 32 ቡድኖች ዋንጫውን ለማንሳት የሚፋለሙ ሲሆን፤ በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ 64 ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ፊፋ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ እንዲያጫውቱ ከመረጣቸው 36 የመሐል ዳኞች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ሲሆን በዓለም ዋንጫው አገሩን ወክሎ በዓለም ዋንጫ ላይ የሚያጫውት የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ዳኛ ነው። የዘንድሮው ይፋዊ የዓለም ዋንጫ ኳስ ቴሌስታር 18 የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች አዲዳስ የተሰራ ነው። በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ዳኝነት(VAR) ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ለዚህም ፊፋ 13 ዳኞችን መርጧል። ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ጀርመንና ቤልጂየም የዓለም ዋንጫውን የማንሳት የቅድሚያ ግምት ያገኙ አገራት ናቸው። በዘንድሮው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ላይ ፓናማ እና አይስላንድ የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋቸውን የሚያደርጉ አገራት ናቸው። የ2018 የሩሲያ ዓለም ዋንጫን በመላው ዓለም ከ3 ቢሊየን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን መስኮት  ያዩታል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም