የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ነው

106
ደሴ ኢዜአ ነሀሴ 24 /2011 በአፋር ክልል በኩል ወደ አማራ ክልል እየገባ ያለውን የአንበጣ መንጋ በቡቃያ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የመከላከያ ስራ እየተካሔደ መሆኑን ተገለፀ ። በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ እንደገለፀው የአንበጣ መንጋው ባለፉት ሁለት ቀናት በአፋር ክልል በኩል በዞኑ ወደሚገኙ አራት ወረዳዎች እየገባ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል ። በመምሪያው የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አራርሳ ወርቅነህ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው ወደ ዞኑ እየገባ ያለው ከየመን ተነስቶ በአፋር ክልል በሚገኙ 7 አጎራባች ወረዳዎች በኩል ነው ። የዞኑ ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በማቀናጀት አሰሳና የቅደመ መከላከል ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ወርቅነህ በተለይ በባቲና ደዌ ሀረዋ ወረዳዎች የአንበጣ መንጋው እየገባ መሆኑን ተረጋግጧል ። መንጋው በቡቃያው ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በባላዊና በዘመናዊ መንገድ ለማስወገድ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ። ከፌደራልና ከክልል የተወጣጡ ባለሙያዎች የአንበጣ መንጋው የሚያድርበትንና የሚያርፍበትን ቦታ በመለየት የኬሚካል ርጭት ለማድረግ የሚያስችል ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ ተብሏል ። የአንበጣ መንጋው በየደቂቃው ስለሚንቀሳቀስ ለርጭት አስቸጋሪ በመሆኑ የማደሪያና የማረፊያ ቦታዎቹ የመለየት ስራው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ። የአንበጣ መንጋ በተፈጥሮው የሚረብሽ ድምጽ ስለማይወድ ህብረተሰቡ ጅራፍ በማጮህ፣ የአምቡላንስ ጨከት በማሰማትና ድምጽ ያላቸውን ቁሳቁሶች በመጠቀምና በሚያርፍበት ቦታ ተከታትሎ በመጨፍጨፍ ለመከላከልና ለማጥፋት እየተረባረበ መሆኑን ተናግረዋል ። ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በዞኑ ስር በሚገኙ ሰባ ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ርብርብ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ ማስወገድ እንደተቻለ ተናግረዋል ። በባቲ ወረዳ የጉሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ አሊ እንዳሉት ሰኔ ወር ላይ ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ የሚረብሽ ድምጽ በማሰማት በባህላዊ መንገድ ጉዳት ሳያድርስ ከማህበረሰባቸው ጋር በመሆን ማስወገድ እንደቻሉ በመግለፅ ሌሎችም ዘዴውን እንዲከተሉ መክረዋል ። በአርጎባ ወረዳ የ06 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኢብራሂም ሰኢድ በበኩላቸው ከግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክር መሰረት ማሳቸውን በየሰዓቱ በመፈተሽና በመጠበቅ አንበጣው እንዳይገባ እየተከላከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። የአካባቢው አርሶ አደሮች መንጋውን ለመከላከል ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅተው ጅራፍ በማጮህ፣ ቁሳቁሶችን በማንኳኳትና የተለያዩ ድምጾችን በማሰማት በባህላዊ መንገድ እየተከላከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ እንደገለፁት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ በ8 ወረዳዎች ተከስቶ የነበረዉን የአንበጣ መንጋ ጉዳት ሳያደርስ ማስወገድ ተችሏል ። በአሁኑ ወቅትም የአንበጣ መንጋው ወደ ዞናቸው እንዳይገባ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የቅኝትና የአሰሳ ተግባር በቀበሌ ደረጃ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና ደቡብ ወሎ ዞኖች በመኸር ከሚለማው ከ500 ሺህ ሄክታር መሬት ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የሚጠበቅ ሲሆኑ ለእቅዱ መሳካት አንበጣውን በቅንጅት መከላከል ያስፈልጋል ተብሏል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም