በምእራብ ሸዋ ዞን ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በቁጠባ ተሰበሰበ

545

አምቦ ሰኔ 7/2010 በምእራብ ሸዋ ዞን የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል እየተሻሻለ በመምጣቱ ባለፉት አስር ወራት  ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በቁጠባ መሰብሰቡን የዞኑ የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ገለፀ ፡፡

የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ አበበ ኡማ ለኢዜአ እንደገለጹት የህበረት ስራ ማህበሩ ከሚሰጣቸው በርካታ አገልግሎቶች መካካል የብድርና ቁጠባ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡

በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ 574 የብድርና ቁጠባ ህብረት ስራ ዮኒዬኖች አማካኝነት ለህብረተሰቡ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ባለፉት 10 ወራትም ከ43 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የብድር አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ ወቅትም 27 ሚሊዮን ብር የቁጠባ ሒሳብ መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

ኤጀንሲው የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ  ወጣቶችን ጨምሮ ከ7 እስከ 12 ዓመት ያሉ ህጻናትም ሳይቀሩ በቁጠባ እንዲሳተፉ ወላጆችን በማግባባትና ግንዛቤ በመፍጠር  ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቆጥቡ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የቁጠባ ክንውኑም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ7 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የብድር ተጠቃሚ የሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎችም በከብት ማድለብ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ፣ በንግድ እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የሚገኙ የብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራት ከ43 ሺህ በላይ አባላትና 38 ሚሊዮን ብር የገንዘበ አቅም ላይ መድረሳቸው ታውቋል ፡፡

በዞኑ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ለ1ሺህ 171 ወገኖች የስራ ዕድል መፍጠራቸው አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

የአምቦ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሚደቅሳ ሹሚ እንዳለው ከሰባት ጓደኞች ጋር “አብዲ ቦሩ” በሚል ስያሜ  ማህበር መስርተው “ከወልታኔ አምቦ” የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ባገኙት ብድር የኮምፒውተር ቤት መክፈታቸው ገልጻል፡፡

ከኮሚፒውተር ቤቱ በሚያገኙት ገቢም ብድራቸውን በመክፈል ላይ ሲሆኑ 5 ሺህ ብር መቆጠባቸውን ተናግሯል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ ብድር በመውሰድ ስራቸውን ለማስፋፋት ማሰባቸውን አመልክቷል፡፡

ባገኙት ብድር እንጀራ ለዩኒቨርሲቲ፣ ለምግብ ቤት እና ለተለያዩ ሆቴሎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ  የጉደቱ ኮምቦልቻ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘበነች ያደቴ ናቸው፡፡

በስራቸውም የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ህይወት በመምራት ላይ እንደሚገኙ አመልክተው 3 ሺህ 500 ብር በቁጠባ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡