የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

560

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ሊያካሄዱ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ከሰኔ 8 እስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ነው የገለጸው።

በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በጋራ ጉዳዮችና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ ይመክራሉ ተብሏል።

ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ጋርም ውይይት እንደሚያደርጉ የተጠቀሰው አልጋ ወራሹ፤ በአገሪቷ የመስክ ጉብኝትም ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሪቱ ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በተለያዩ መስኮች እያፈሰሱ ሲሆን በቀጣይም በግብርናና ቱሪዝም ዘርፍ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ይፈለጋል። በዚህም ላይ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዝዳንቱ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።