በድሬዳዋ የጣለው ከባድ ዝናብ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

89
ድሬዳዋ/ኢዜአ/ ነሐሴ 22/2011 … በድሬዳዋ ከተማ ትናንት የጣለው ከባድ ዝናብን ተከትሎ አንድ ሰው በመብረቅ ህይወቱ ሲያልፍ በሌሎች ሶስት ሰዎችና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ ። የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ቡድን አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር ባንተአለም ግርማ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው ትናንት የጣለውን ሃይለኛ ዝናብ ተከትሎበወረደው መብረቅ  ገንደ ጋራ በተባለ ሰፈር አንድ ሰው ጭንቅላቱን ተመትቶወዲያውኑ ህይወቱን አልፏል ። በተጨማሪም አንድ ባለሦስት ጎማ ታክሲ መንገድ ሲያቋርጥ በደራሽ ጎርፍ ተገልብጦ በሶስት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል ። እንደረዳት ኢንስፔክተሩ ገለፃ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በድልጮራ ሆስፒታል ህክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  አገልግሎት የድሬዳዋ አስተዳደር አውቶሜሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ዘመድሁን እንደገለፁት ደግሞ ትናንት ማታ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ። የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ የእንጨትና የኮንክሪት ምሰሶዎች ማፈራረሱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ። በተለይ በከተማው ከዚራና ነምበርዋን አካባቢው የሚገኙ ትልልቅ የዛፍ ግንዶች በንፋስ በመገንጠላቸው የኤሌክትሪክ መስመሮች ተበጣጥሰው አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ የኤክትሪክ ሰራተኞች ከትናንት ማታ ጀምሮ ባደረጉት ርብርብ አገልግሎቱእንዲጀምር መደረጉንም አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል ። የከተማው ነዋሪዎች ግን በጊዜያዊ ጥገናዎች ላይ ከመረባረብ ይልቅ ያረጁ መስመሮችን በማስተካከል ዘላቂ መፍትሄ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል ። ወይዘሮ ረምላ አህመድ የተባሉ የከተማውነዋሪ እንደገለፁት በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት ከኢንተርኔት አገልግሎት መስጫ ተቋማቸው ማግኘት የሚገባቸው የዕለት ገቢ እንዳሳጣቸው ተናግረዋል፡፡ የኮኔል ሰፈር ነዋሪ አቶ ሰለሞን በዛብህ ንፋሱ በአካባቢያቸው  8 የኤሌክትሪክ ተሸካሚ የእንጨት ምሰሶዎችን ከጥቅም ውጪ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ የከተማው ኤሌከትሪክ  ኃይል ለበሰበሱ የእንጨት ምሰሶዎች ዘላቂ መፍትሄ አንዲፈልግም ጠይቀዋል ። በኤሌክትሪክ አገልግሎት    የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ ዲስትሪቢዩሽን፣ ኮንስትራክሽን፣ኦፕሬሽንና ሜንተናንስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ወልደገብርኤል ስለሁኔታው ተጠይቀውየእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመቀየር ስራ እየተካሄደ በመሆኑ በቅርቡ ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ብለዋል ። እስከ አሁን ድረስም በኢንዱስትሪ መንደር ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መስመር መቀየሩንም ተናግረዋል፡፡ ትናንት የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ በመሠረተ ልማት አውታሮቹ ላይ ያጋጠመ ጉዳት የለም ብሏል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም