ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኮርያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ጃፓን አቀኑ

72
ነሀሴ 21 / 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሁለት ቀናት የደቡብ ኮርያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደጃፓን አቅንተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮርያ ቆይታቸው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢን ጋር በመገናኘት የሁለቱ አገራት ወዳጅነት በሚጠናከርበት መንገድ መክረዋል። አገራቱ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች የተፈራራሙ ሲሆን፤ የጋራ የሚንስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋምም ወስነዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በተጨማሪ የኮርያ ወጪና ገቢ (ኤክዚም) ባንክና የኮርያ ዓለማቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ፕሬዝዳንቶች  ጋርም ምክክር አድርገዋል። ከባንኩ ጋርም የ86 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈርሟል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ የኮርያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁም በ7ኛው የቶኪዮ የአፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ (ቲካድ) ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ጃፓን አቅንተዋል። የጃፓኑ ጉባኤ የባለ ብዙ ወገን መድረክ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የግል ኩባንያዎች፣ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል። ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተጨማሪ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በጉባኤው ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጉባኤው "በህዝብ፣ ቴክኖሎጂ ፈጠራ የአፍሪካን ልማት እናፋጥን" በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ነሃሴ 22 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል። የተባባሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ)፣ የዓለም ባንክና የአፍሪካ ህብረት ደግሞ የጉባኤው ተባባሪ አዘጋጆች ናቸው። የመጀመሪያው የቲካድ ጉባኤ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጣር በ1993 ነው የተካሄደው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ከጉባዔው ጎብ ለጎን ከጃፓን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም