ህብረተሰቡ ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን የመፍታት ባህሉን ሊያዳብር ይገባል-አስተየያት ሰጪዎች

1316

ሰኔ 7/2010 ህብረተሰቡ ለሁከትና ብጥብጥ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ባህሉን ሊያሳድግ እንደሚገባው በአዲስ አበባ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በሀገሪቱ ለ2ኛ ጊዜ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት በተለያየ ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ሳያመሩ ህብረተሰቡና የመንግሥት አካላት በውይይት  መፍትሄ ሊያበጁላቸው ይገባል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በእለት ከዕለት ስራዎቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረው እንደነበርም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት መምህርና በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶች  የማማከር አገልግሎት የሚሰጡት  አቶ ኢሳያስ አለሙ እንዳሉት  አዋጁ  በሀገሪቱ የቱሪዝም  ዘርፍ ላይ መቀዛቀዝ ፈጥሯል፡፡

ዘርፉ በባህርይው የሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ወደማያውቁት ሀገርና አካባቢ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ በመሆኑ በሰላምና መረጋጋት ይፈልጋል፡፡

በተለይ ካደጉ ሀገራት የሚመጡ ጎብኝዎች የሀገራቸው መንግሥት የመዳረሻ ሀገራትን ሰላምና ጸጥታ መሰረት በማድረግ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን የሚያስተላልፍ በመሆኑ ጎብኝዎች ደፍረው የጸጥታ ችግር ወዳለባቸው ሀገራት እንደማይመጡም ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ኢሳኢያስ እንዳሉት “በሀገሪቱ አበረታች  ገቢ ይገኝብት የነበረው  የኮንፍረንስ ቱሪዝም  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ምክንያት  መቀነሱ አይቀርም፤ በሆቴሎች  በስፋት ሲጠቀሙ ይታዩ የነበሩ  ቱሪስቶች  ቁጥርም  እንዲሁ˝፡፡

ሀገሪቱ ተደጋጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስታውጅ  ዓለም ዓቀፍ እውቅናዋ  እየደበዘዘ ስለሚሔድ ጎብኚዎች ጎረቤት ሀገራትን ምርጫቸው ለማድረግ እንደሚገደዱ የገለጹት አቶ ኢሳኢያስ  ይህም ሀገሪቱ ከዘርፉ በምታገኘው ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር አብራርተዋል፡፡

አቶ ኢሳኢያስ እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ያስተላለፉትን መልዕክት ህብረተሰቡ በአግባቡ ተገንዝቦ  የሀገሩን እና የራሱን ሰላም መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ድርጅት የለውጥ ስራ አመራር አስተባባሪው አቶ የማነ ተካም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ለውጪ ጎብኝዎች “የእደ ጥበብ ውጤቶችን በመሸጥ የምናገኘውን ገቢ ቀንሶብናል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት የታየው አንጻራዊ ሰላም በስራቸው ላይ የተሻለ መነቃቃትን እንዳመጣላቸው ገልጸው የአስቸኳ ጊዜ አዋጁ መነሳት ደግሞ የተሻለ እድል ይዞላቸው እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡

በግል የስራ ዘርፍ የሚተዳደሩት አቶ ሚኪያስ ቸሩ በበኩላቸው ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥረውንና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ የሚበረክተውን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እንዳለ ሆኖ ህብረተሰቡ ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ አለመግባባቶችን አስቀድሞ የመፍታት ባህሉን ማዳበርና በየአካባቢው ሰላሙን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለሁከትና ብጥብጥብ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ መልካም አስተዳደርና ከፍትህ ስርዓቱ ጋር የተያያዙ ችግርችን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23/2010 ዓ.ም ያጸደቀውን የአስኳይ ጊዜ አዋጅ ግንቦት 28/2010 ማንሳቱ ይታወሳል፡፡