በጉጂ ዞን ደረሰኝ ከማይሰጡ የንግድ ድርጅቶች ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አልተሰበሰበም

90
ነገሌ (ኢዜአ) ነሀሴ 20 ቀን 2011 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ደረሰኝ ከማይሰጡ የንግድ ድርጅቶች ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱን የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የግብር ሥወራው ከገቢዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤት ሠራተኞች ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር ማነስ የተፈጠረ መሆኑን አንዳንድ የነገሌ ከተማ ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡ የጉጂ ዞን ገቢዎች የባለስልጣን ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሀብታሙ ገብረሀና ለኢዜአ እንዳሉት የግብር ስወራውን ለመከላከል በ426 የንግድ ድርጅቶች ላይ ጥናትና ክትትል ተደርጓል፡፡ “በእዚህም ህጋዊውን መስመር ተከትለው ለተጠቃሚዎች ደረሰኝ በመስጠት ሲሰሩ የተገኙት 96 የንግድ ድርጅቶች ብቻ መሆናቸው ታውቋል” ብለዋል፡፡ የጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራው የንግድ ድርጅቶቹ የእለት ተዕለት ገቢና የወጪዎችን መረጃ አያያዝ መሰረት አድርጎ በጥንቃቄ የተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በእዚህም ለመንግስት መክፈል የነበረባቸውን ግብር ለመሰወር የሞከሩ 330 የንግድ ድርጅቶች የእለት ገቢያቸውን በመደበቅ፣ 105ቱ ደግሞ ለተጠቃሚዎች የቫት ደረሰኝ ሳይሰጡ ሲሰሩ እንደተደረሰባቸው አቶ ሀብታሙ አመልክተዋል፡፡ በዚህ ዓመት የንግድ ድርጅቶቹ የመንግስት ግብር ለመሰወር ባደረጉት ሙከራ 14 ሚሊዮን 950 ሺህ ብር የሚገመት ገቢ ሳይሰበሰብ መቅረቱን አስረድተዋል። “ድርጅቶቹ ለመንግስት መግባት የሚገባውን ገቢ ለመሰወር ባደረጉት ሚከራ እንደየጥፋት ደረጃቸው ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል” ብለዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የጥፋት ደረጃቸው ከፍ ያለና የቫት ደረሰኝ ሳይሰጡ ሲሰሩ የተገኙ 105 ነጋዴዎች 3 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር መቀጣታቸውንም ተወካዩ አመልክተዋል፡፡ ዓመታዊ ገቢን መደበቅና ለተጠቃሚዎች የቫት ደረሰኝ ሳይሰይሰጡ መስራት ከ3 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ ውል ስምምነት ላይ ተቀምጧል፡ አቶ ሀብታሙ እንዳሉት ያልተሰበሰበውን ገንዘብ ለመሰብሰብና ግብር የሰወሩ የንግድ ድርጅቶችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከፍትህ አካላት ጋር በመነጋገር ላይ ናቸው። ጽህፈት ቤቱ ዘንድሮ ከመደበኛ ገቢ ለመሰብሰብ በዕቅድ ከያዘው 269 ሚሊዮን 742 ሺህ ብር በ14 ሚሊዮን 152 ሺህ ብር ብልጫ ያለው ገቢ ለመሰብሰብ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡ ግብርን በታማኝነትና በፍትሀዊነት መክፈል ሀገራዊ የዜግነት ግዴታን መወጣት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በነገሌ ከተማ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ መኮንን ንሳኮ ናቸው፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ማነስ በነገሌ ከተማ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር እንዲቃዘቀዝና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እየተስፋፋ እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ “የተጣለብኝን 4 ሺህ ብር ዓመታዊ ግብር በወቅቱ በመክፈል እየሰራሁ ነው” ያሉት አቶ መኮንን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ በእዚሁ ከተማ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መስፍን ጥሩነህ በበኩላቸው የግብር ስወራንና ህገወጥ ንግድን የሚያስቀር አሰራር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡ ህገ ወጥ ንግድ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ከማሳጣት ባለፈ ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰብ እንዳይቀርብ እንቅፋት መሆኑንም አስረድተዋል። ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለክትትልና ቁጥጠር ስራ የሚመደቡ ባለሙያዎች በፍትሀዊ የግብር አወሳሰንና በህገ ወጥ ንግድ ስራ ላይ ያላቸው አቋም ጠንካራ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም