መቐለ 70 እንደርታ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለም

146

ነሀሴ 19/2011  በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከኢኳቶሪያል ጊኒው ካኖ ስፖርት አካዳሚ ያደረገው መቐለ 70 እንደርታ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። መቐለ 70 እንደርታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት በመለያየቱ በድምር ውጤት 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

መቐለ 70 እንደርታ በ11ኛው ደቂቃ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ግብ መሪነቱን መያዝ ቢችልም ቤንጃሚን ናኦኔ በ37ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ካኖ ስፖርት አካዳሚን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከዚህ በኋላ መቐለ 70 እንደርታ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማውሊ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

መቐለ 70 እንደርታዎች በጨዋታው አሸንፈው መውጣት የሚችሉባቸውን ግልጽ የግብ እድሎች በተደጋጋሚ ቢያገኙም መጠቀም ባለመቻላቸው ከአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕድላቸውን አምክነዋል።

መቐለ 70 እንደርታ በኳስ ቁጥጥርና ተጭኖ በመጫወት ከተጋጣሚው ካኖ ስፖርት አካዳሚ የተሻለ የነበረ ሲሆን ካኖ ስፖርት አካዳሚ በጨዋታው የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ስልትን በመጠቀም ተጫውቷል።

ጅቡቲያዊው የመሐል ዳኛ ሳዳም መንሱር ሁሴን ለመቐለ 70 እንደርታ ሁለት ለካኖ ስፖርት አካዳሚ ሶስት ተጫዋቾች የቢጫ ካርድ አሳይተዋል።

የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አማኑኤል ገብረሚካኤል መቐለ 70 እንደርታ ከሜዳው ውጪ 2 ለ 1 ሲሸነፍ እና ዛሬ ክለቡ አቻ ሲወጣ ሁለቱንም ግቦች በማስቆጠር የክለቡን ታሪካዊ የአህጉራዊ መድረክ ግቦች ማስቆጠር ችሏል።

ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው ካኖ ስፖርት አካዳሚ በቀጣይም ከግብጹ አል-አህሊ ጋር በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም የሚጫወት ይሆናል።

ትናንት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ታንዛንያ ላይ ያደረገው ፋሲል ከነማ በተጋጣሚው አዛም 3 ለ 1 የተሸነፈ ሲሆን በድምሩ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ለአዛም ሪቻርድ ጆዲ ሁለት ጎሎችን ኦብሬይ ቺርዋ የተቀረውን ጎል ሲያስቆጥር ሙጂብ ቃሲም የፋሲል ከነማን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል።