የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ማእቀፍ አለመኖር ሀብቱ ለከፋ ጉዳት እየተጋለጠ መሆኑ ተገለፀ

1485

አዳማ ሰኔ 7/2010 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖር ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት እንቅፋት መፍጠሩን የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል የመሬት አጠቃቀም መሪ እቅድ አፈጻጸም ላይ የሚመከር አውደ ጥናት ትናንት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት  የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንዳስታወቁት የመሬት አጠቃቀም ሥርዓቱን በተሻለ አቅም ለመገንባት ስትራቴጂ ዕቅድ ተነድፎለት መተግበር ቢሞከርም ዘርፉን የሚመራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በመሬት ሀብቱ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው።

በአጠቃላይ የፖሊሲው አለመኖር የእርሻ መሬቶችን ጨምሮ የውሃ አዘል አካባቢዎች፣ የደን መሬቶች፣ ትኩረት የሚሹ የብዝሀ ህይወት ሀብቶች፣ በተፈጥሮ መስህብነታቸው የታደሉና ከፍተኛ የቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ ፓርኮች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከማድረግ  ባለፈ ለከፋ መራቆት እየተጋለጠ ነው።

በዕቅድ ባልተመራ የከተሞችና መሰረተ ልማቶች መስፋፋት ምክንያትም ለድህነት ቅነሳ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች በሀገር ደረጃ ለመፍታት እንዲቻል የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ዝግጅት ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀ ሲሆን የፖሊሲ ማዕቀፍም በረቂቅ ደረጃ መዘጋጀቱን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

”የመሬት አጠቃቀም እቅድ ዝግጅት ከፍተኛ ልምድ፣ ብቃትና የቴክኒክ አቅም ያለው የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ ከፍተኛ የሀብት ምንጭና ይህንን እቅድ ለመተግበርና ለመምራት የሚችል ተቋማዊ አደረጃጀትም ይፈልጋል” ብለዋል።

በመሆኑም የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት የሚዘረጋና የሚያስተባብር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በፌዴራል ደረጃ በመደራጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

”ይህም ውስን የሆነውን የመሬት ሀብታችንን በየዘርፉ በማልማት የተከሰቱትን የመሬት አጠቃቀም ግጭቶችና ሽሚያ በማስተካከል የተሻለ የአጠቃቀም ሥርዓት በዘላቂነት የመዘርጋት እድል እንደሚሰጥ ታምኖበታል” ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው በክልሉ የገጠር መሬትን አግባብ ከሌለው አጠቃቀም ለመታደግ የመሬት አጠቃቀም መሪ እቅድ ጥናት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥናቱ ለግብርና፣ ለግጦሽ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም ልማቶች እንዲሁም ለትምህርት፣ ለጤና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለሌሎችም መሰረተ ልማቶች የሚውለውን መሬት ለይቶ በመከለል ለታለመላቸው አላማ ብቻ እንዲውሉ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ነው።

ይኽው የመሬት አጠቃቀም መሪ እቅድ ጥናት  ስራ እስካሁን 80 በመቶ መከናወኑን ገልጸው ቀሪውን እስከ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ድረስ በማጠናቀቅ ለትግበራ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለመሪ የመሬት አጠቃቀም እቅድ ዝግጅት ልዩ ትኩረት በመስጠት  ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው በሀገር አቀፍ ደረጃ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩ ስራ ላይ ለማዋል እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

መድረኩም የክልሉ መሪ የመሬት አጠቃቀም አፈጻጸም ላይ በመወያየት ለሚቀጥለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የመፍትሄ ሀሳብ ለማሰባሰብ ታስቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከክልሉ፣ ከዞንና ከፌዴራል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።