በጋምቤላ ክልል ለግብርና ኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች ፈጥነው ሥራ እንዲጀምሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠየቁ

59
ጋምቤላ ነሐሴ 19 ቀን 2011በጋምቤላ ክልል ለግብርና ኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱ ባለሃብቶች ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቀረበ። በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት መሬት የተረከቡ 285 ባለሃብቶች ከአካባቢው እንደተሰወሩ ተገልጿል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ሰሞኑን በአበቦ ወረዳ የባለሃብቶችን እርሻ በጎበኙበት ወቅት እንዳሳሰቡት  ኢንቨስትመንት ለአገር ልማት ያለውን ድርሻ በመገንዘብ መሬት የተሰጣቸው ባለሀብቶች ሥራ ፈጥነው መጀመር ይጠበቅባቸዋል። በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ከገቡት ከ700 በላይ ባለሃብቶች መካከል 285ቱ መሬት ተረክበው መሰወራቸውን ተናግረዋል። የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለአገር ልማትም ሆነ ለዜጎች ሥራ ለመፍጠር ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የክልሉ መንግሥት የባለሃብቶች ችግሮች ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም አልሚ ባለሃብቶች በመደገፍ ረገድ የክልሉ መንግሥትና በየደረጃው ያለው አመራር በትኩረት ይሰራል ብለዋል። የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ኡጁሉ ኡሞድ በበኩላቸው በክልሉ በተለይም በግብርና ኢንቨስተመንት ለመሰማራት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች አብዛኛዎቹ መሬት ተረክበው ከሶስት ዓመታት በላይ መሰወራቸውን ተናግረዋል። ኤጀንሲው አልሚ ባልሆኑ ባለሃብቶች የተያዘው መሬት ወደ መንግሥት ተመላሽ እንዲሆን ለክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርዱ የውሳኔ ጥያቄ ቢያቀርብም፤ ቦርዱ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ማድረጉን ተናግረዋል። ኤጀንሲው እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2011 ባለው ጊዜ የጠፉት ባለሃብቶች ቀርበው ጉዳያቸውን ማስረዳት ካልቻሉ የያዙት መሬት ተመላሽ ሆኖ ለሌሎች ባለሃብቶች የሚተላለፍ ይሆናል ብለዋል። መሬት መያዝ ያለበት ''በልማት አርበኛ ባለሀብቶች'' ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ኤጀንሲው ለአልሚ ባለሃብቶች ድጋና እውቅና እንደሚሰጥ ልጸዋል። በወረዳው በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት ባለሃብቶች መካከል የዘሩ ገብረሊፋያኖስ የእርሻ ልማት ተወካይ አቶ ሮቤል ገብረሊፋያኖስ አካባቢው ለግብርና ልማት ምቹ በመሆኑን ተጠቃሚ ሆነናል ይላሉ። ከገበያ በስተቀር በአካባቢው ችግር ያለመኖሩን ተናግረዋል። በክልሉ ከውጭ የገቡትን ሳይጨምር ከ700 ለሚበልጡ ባለሃብቶች ከ600 ሺህ ሄክታር መሬት ለባለሃብቶች መተላለፉን የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም