በጋምቤላ ክልል አመራር የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለልማት እንዲያውል ተጠየቀ

173

ጋምቤላ ነሐሴ 19 /2011 በጋምቤላ ክልል በየደረጃው የሚገኘው አመራር የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለልማት እንዲያውል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ።

ከክልል እስከ ወረዳ ለሚገኙ የአመራር አካላት በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና በጋምቤላ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑሞድ ኡጁሉ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት የክልሉን ሕዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልገሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ይገባል።

የክልል የፋይናንስ አስተዳደርና የበጀት አጠቀቀም ሥርዓት ችግሮች ስላሉበት የልማት ዕቅዶች በተፈለገው ደረጃ ግባቸውን እየመቱ አይደሉም ብለዋል።

በተለይም በወረዳዎች የሚታየው የሀብት አጠቀቀምና የገቢ አሰባሰብ ችግሮች በልማት ሥራዎች አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከክልል እስከ ወረዳ ጠንካራ የፋይናንስ አስተዳደርና የበጀት አጠቀቀም ሥርዓት በመዘርጋት በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት እንዲሰሩ አቶ ዑሞድ አሳስበዋል።

ስልጠናው  አመራሩ በፋይናንስ አስተዳደርና በጀት አጠቀቀም ያለው ግንዛቤ በማሳደግ በቀጣይ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኡማን አሙሉ በበኩላቸው በክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በበጀት አጠቀቀም፣ በንብረት አያያዝና በውስጥ ኦዲት ቁጥጥርና ክፍተቶች እንዳሉባቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም እንዚህን ክፍተቶች በማረም የሕዝብና የመንግሥትን ሀብት ለልማት እንዲውል አመራሩ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር አቶ ኡቻላ ቻም በሰጡት አስተያየት በክልሉ ከግዥ፣ ከጥሬ ገንዝብና ሌሎችም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በሚታዩት ክፍተቶች በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጠናው በታገዘ መንገድ በመንቀሳቀስ ሀብቱን በሥራ ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን እስከ ታቸኛው መዋቅር ለመተግበር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ አቶ ዓለማየሁ ዋይዋይ የተባሉ የስልጠና ተሳታፊ ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በጥሬ ገንዝብ አስተዳደር፣ በመንግስት ፋይናንስ የሕግ ማዕቀፎች፣በግዥና ንብረት አስተዳደርና በተዛማጅ ርዕስ ጉዳዮች ስልጠናው ሰጥተዋል።