ቅድመ ዝግጅቱ በእውቀትና በስነምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት ያግዛል

123

ነሐሴ 19/2011 በመዲናዋ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች እድሳትን ጨምሮ ሌሎች እየተሰሩ ያሉ ቅድመ ዝግጅቶች በእውቀትና በስነምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ይነገራል።

የኢዜአ ሪፖርተር በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ በከተማዋ ያሉ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ምቹ የመማር ማስተማር ሥራን የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የቤተልሄም ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር አቶ ሰይፌ ስለሺ እንዳሉት ለትምህርት ቤቱ እየተደረገ ያለው እድሳት በተማሪዎችና በመምህራን ላይ የሚፈጥረው መነቃቃት ለመማር ማስተስተማር ሂደትና ለትምርት ጥራት መሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

የትምርት ቤት ቀዳሚ አላማዎች ተማሪዎችን በእውቀትና በስነምግባር ማነጽ ነው ያሉት አቶ ሰይፌ፤ እድሳቱ ለዘርፉ ትኩረት ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን ከመፍጠር አንጻር አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ።

በትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ የስነ-ልቦና መምህራን መኖራቸውን ገልጸው፤ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ለማስተካከልም ያግዛል ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ የአማርኛ ቋንቋ መምህር አብረሃም በቀለ ለትምህርት ቤቶች እየተደረገ ያለው ዝግጅት እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ መጭውን የትምህርት ዘመን በተነቃቃ ስሜት ለመቀበል ያስችላል ብለዋል።

ስነምግባር ከአለባበስ ይጀምራል ያሉት መምህር አብረሃም፤ በትምህርት ቤቱ ደንብና ስርዓት መሰረት ተማሪዎች የደንብ ልብስ መልበስ እንዳለባቸው ና ከትምርታቸው እንዳይዘናጉም ሞባይልና የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ መያዝ እንደማይፈቀድላቸውም ጠቅሰዋል።

በትምርት ቤቱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ወላጅ እናት ወይዘሮ ፍሬ ዘነበ እንደሚሉት፤ ተማሪዎች በጊዜያዊ ነገር እንዳይታለሉና ከትምህርታቸው እንዳይዘናጉ ወላጆች ተገቢወን ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በእውቀትና በአእምሮ የዳበረ ትውልድን  ማፍራት  ከሀገር ግንባታ ተለይቶ አይታይም ያሉት ወይዘሮ ፍሬ፤ ለተማሪዎች ውጤታማነት ከመምህራን ጥረት ጎን ለጎን የወላጆች እገዛ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።

የእቴጌ መነን ርዕሰ መምህር አቶ መሃመድ ሃሰን ትምርት ቤቱ በ2012 የትምርት ዘመን ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት መቀየሩን ጠቅሰው ለዚህም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች ትንሽ ሰርተው መዝናናትን ስለሚያበዙ በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ያሉት ርእሰ መምህሩ፤ በአዳሪ ትምህርት ቤት ሙሉ ጊዜአቸውን ስለሚጠቀሙና በአንጻራዊነት የተሻለ ግብአት ስለሚያገኙ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡

በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ከ9-12 ክፍል ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ገልጸው፤ የተሻለ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ተወዳድረው እንደሚገቡ በማድረግና  የተሻለ ብቃት ያላቸው መምህራንን በመመደብ የትምርት ጥራትን ለማስጠበቅ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ይደረጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ትምርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት እዳሉት፤ ከተማ አስተዳደሩ ለ2012 የትምህርት ዘመን ከትምህርት ቤቶች እድሳት ባለፈ ለተማሪዎችና መምህራን የትምህርት ግብአቶችን እያቀረበ ነው።

በሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ደብተርና የደንብ ልብስ እንደሚቀርብ ገልጸው ለመምህራን ደግሞ ጋወን፣ ቦርሳና ታብሌት ይሰጣል ብለዋል።

የመምህራንን አቅም ለማጎልበትም በክረምት፣ በማታና  ቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብሮች የትምህርት ደረጃዎችን እንዲያሻሽሉ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዲማሩ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በዚህም 1ሺህ የቅደመ በደበኛ መምህራን፣ 92 የትምህርት ቤት አመራሮች ና 243 የሁለተኛ ደረጃ መምህራን የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ተደርጓል ነው ያሉት።

በሚኖሩበት አካባቢ እንዲሰሩም ለ391 መምህራን ዝውውር መፈጸሙን የገለጹት አቶ አበበ፤ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የራሱ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

በከተማ ደረጃ በአዲሱ የትምህርት ዘመን እስከ ስምተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በማመቻቸት 300ሺህ ተማሪዎች የእድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የገለጹት።

በዚሁ ትምህርት ዘመን ሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶች መቋቋማቸውን የጠቀሱት አቶ አበበ፤ መነን የሴቶች፤ አቃቂ ደግሞ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሆነው እያንዳንዳቸው 500 ተማሪዎችን እንደሚያስተናግዱም  አብራርተዋል፡፡