በመቀሌ የተከበረው የአሽንዳ በዓል ተጠናቀቀ

168
መቀሌ  ነሐሴ 19 / 2011 በመቀሌ ከተማ ለሦስት ቀናት የተከበረው የአሽንዳ በዓል ትናንት ምሽት ተጠናቀቀ። በዓሉን በድምቀትና በሰላማዊ መንገድ እንዲከበርና ለሌሎች በማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት ደግሞ የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል። በዓሉን በሺህዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ ደምቀውና ተውበው ባህላዊ ጭፈራዎችና ዘፈኖች አክብረውታል። የመቀሌ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ቱሪስቶችና ዳያስፖራዎች የበዓሉ ታዳሚዎች ነበሩ። እንዲሁም ከአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች፣ከአዲስ አበባ ከተማና የአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የመጡ እንግዶች የበዓሉ ተከፋይ ሆነዋል። በትግራይ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ''የዘንድሮው የአሸንዳ በዓል በሕዝቦች መካከል የቆየውን አንድነትን፣ሰላምና ልማትን ይበልጥ እንዲጎለብት በሚያንጸባርቅ መልኩ ተከብሯል’’ ብለዋል። በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ በተለይ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በበዓሉ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ብርቅዬ በዓል የሆነውን የአሸንዳ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገቡትን ቃል ተግባራዊ እንደሚያደርጉት እተማመናለሁ ያሉት ኃላፊው፣ዕቅዱ ከዳር እንዲደርስ የበዓሉ ዋንኛ ባለቤቶች ባህሉን እንዲጠብቁ አሳስበዋል። በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶችና ሴቶች የሚጎናጸፉትን ነጻነት ቀጣይነት እንዲኖረውና ከሚደርስባቸው የወንዶች ጥቃትና በደል እንዲላቀቁ ሕዝቡ  ድጋፍ እንዲያደርግም አስገንዝበዋል። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረመድህን በበኩላቸው በዓሉን በተባባሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማሳካት ልጃገረዶች ጥቃቅን የሚመስሉና ባህሉን ከሚበርዙ አለባበስና ድርጊቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጠይቀዋል። በዓል በድምቀት እንዲከበርና በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ተቋማት፣የጸጥታ ኃይሎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ተቋማት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። እንዲሁም በዓሉን ለማድመቅና ጥንታዊ ትሩፋቱን ጠብቆ እንዲሄድ በልጃገረዶች መካከል በቡድን በተደረገው ውድድር ላታዳጊ ህጻናትና አዋቂዎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ላጠናቀቁ ከ7 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር ተሸልመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም