የኢትዮጵያ የምርጫ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ፀደቀ

553

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 18/2011  የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ፀደቀ።

አዋጁ ዓለምአቀፍ የምርጫ ምርሆችን ያካተተ ነው ተብሏል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ሶስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ነው የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ የጸደቀው።

አዋጁ በአገሪቱ በየደረጃው የሚደረጉ ምርጫዎች ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆኑ ያስችላል ነው የተባለው።

ምክር ቤቱ ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓም ባካሄደው 48ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ወደ ህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል።

በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ መሰረት ዛሬ ቋሚ ኮሚቴው የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ እንዳሉት አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የተለያየ ሀሳብና አመለካከት በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመራጩ ህዝብ እንዲያሳውቁ ያስችላል።

መራጩ ህዝብም በመረጃ ላይ በመመስረት በነጻነት ወኪሎቹን የሚመርጥበት የምርጫ ስርዓት መዘርጋት ያስችላል ነው ያሉት።

አዋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ በግልጽ የሚያሳይ የምርጫ ስነ-ምግባር እንዲከተሉ የሚያደርግ እንደሆነም ነው የተብራራው።

ቋሚ ኮሚቴው ከቃላት ጀምሮ የተለያዩ የሀሳብ ማሻሻያዎችን ያደረገ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላትም መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተው ውይይት ተደርጎበታል።

በተለይም በረቂቅ አዋጁ ሴትና ወንድ እኩል ድምጽ ቢያገኙ ሴቷ በምርጫ እንድታሸንፍ በሚደነግገው አንቀጽ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ክርክር አድርገውበታል።

ሴቶች በስራና በትምህርት ከወንዶች ጋር ተወዳድረው እኩል ውጤት ቢያመጡ ቅድሚያ ሰሴቶች የሚሰጠው ዕድል በምርጫ ህግ ተግባራዊ መደረግ የለበትም ህገ-መንግስቱንም የሚጻረር በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል የሚለው ሀሳብ በድምጽ ብልጫ ማሸነፉ አንቀጹ እንዲሻሻል ተወስኗል።

በአዋጁ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ የ10 ሺህ አባላት ድጋፍ ማግኘት ሲኖርበት የክልል ፓርቲዎች ደግሞ አራት ሺህ አባላት ድጋፍ ይጠየቃሉ።

በሌላ በኩል የመንግስት ሰራተኛ በምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ሲቀርብ የምርጫ ቅስቀሳ በሚካሄድበትና ምርጫ በሚከናወንበት ጊዜ ያለ ደመወዝ ፈቃድ እንዲሰጠው ይደረጋል።

ከዚህ ባለፈም በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ ምክር ቤቶች የምርጫ እንቅስቃሴ በሚሳተፍበት ጊዜ በቀጣሪው የመንግስት መስሪያ ቤት ንብረት መገልገል አይፈቀድለትም።

በአዋጁ የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን የሚመለከቱ የስነ-ምግባርና የአፈጻጸም መርሆዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት የሚወሰን መሆኑም ተቀምጧል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር ረቂቅ አዋጅን በአዋጅ ቁጥር 1262/2011 በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።