ባንኩ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግና ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት ይኖርበታል

203

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 18/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግና ተወዳዳሪ ለመሆን በአሁኑ ወቅት የሚታዩበትን ችግሮች ለመፍታት መስራት እንደሚኖርበት ተገልጋዮች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በባንክ የሥራ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሆነውና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱት የንግድ ባንኮች ሁሉ ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ነው ደንበኞች የሚናገሩት።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለፁ የባንኩ ደንበኛ ተቋማት ሰራተኞችና ኃላፊዎች እንደተናገሩት የኔትወርክ መቆራረጥና ከእርሱው ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉት የአገልግሎት ክፍተቶች ሊፈቱ ያልቻሉ የባንኩ ችግሮች ናቸው።

በተለይም ባንኩ በቅርቡ ውሃን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ክፍያ የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩ ችግሩን እንዳባባሰው አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ።

ይህም ተገልጋዮች አላስፈላጊ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን በመጠበቅ የሥራ ጊዜያቸውን ለማጥፋት እንደተገደዱ፤ ጥበቃውም ለእንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን የባንኩ ደንበኞች አመልክተዋል።

በመሆኑም ባንኩ ደንበኞችን በአግባቡና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል በቴክኖሎጂና በአሰራሮች የተደገፈ አቅም መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል።

አለበለዚያ የደምወዝ ክፍያን ጨምሮ በብዛት የያዛቸውን አንዳንድ የክፍያ መሰብሰብ አገልግሎቶች ለሌሎች የተመረጡ ባንኮች ማካፈል የሚቻልበትን መንገድ መዘየድ አለበትም ሲሉ መክረዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፋይናንስና ግዢ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን እጅጉ እንደሚሉት በባንኩ በኩል በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ሰራተኞች ደሞዛቸውን በወቅቱ ማግኘት አልቻሉም፤ ይህም በመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።

ባንኩ አገልግሎት አሰጣጡን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ማደራጀት ይኖርበታልም ብለዋል።

አቶ ሰለሞን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ተወዳዳሪ የሆኑ የግል ባንኮች እየተስፋፉ በመሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚሰጣቸው የአገልግሎት ዓይነቶች መካከል የተወሰኑትን በጥናት በመለየት በሌሎች ባንኮች በኩል እንዲሰጡ ቢደረግ ጫናውን ያቃልላል ሲሉ ተናግረዋል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስኪያጅ አቶ ያብስራ ከበደ ባንኩ የአገልግሎት አሰጣጥ አድማሱን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከደንበኞቻቸው የሚሰበስቡት ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ይፈፀምላቸው ዘንድ ስምምነት መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይም ከሌሎች ተቋማት ጋር መሰል  ስምምነቶች ይፈፀማሉ ብለዋል።

በቅርቡ የተቋማት አገልግሎት ክፍያ የመሰብሰብ ሥራው በተጀመረበት ወቅት የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር መከሰቱን አስታውሰዋል።

ወቅቱ የደሞዝ ክፍያ ወቅት ጭምር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት መፍጠሩን ገልፀዋል።

ሆኖም ባንኩ በርካታ መዋእለ ነዋይ በማፍሰስ ዘመናዊ የክፍያ አማራጮችን ስራ ላይ ያዋለ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ይመቻቻል ነው ያሉት።

እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ባንኩ የገነባው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት እስከ 10 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ደንበኞች ማሰተናገድ የሚችል አቅም አለው።

ባንኩ የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር በሚፈጠርበት ወቅትም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን በፍጥነት ችግሩ እንዲፈታ እንደሚሰራም አቶ ያብስራ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ 450 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ግዙፍ ባንክ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ቁጥር 22 ሚሊዮን መድረሱን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።