የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃትን ለመፍጠር ምክክር ሊደረግ ነው

87

ነሐሴ 17/2011 የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ አልፎ አልፎ በተከሰተው አለመረጋጋት የተቀዛቀዘውን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ምክክር ሊያደርጉ ነው።

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህም የቱሪዝም ዘርፍ በዋናነት  ሰላምን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ሲከሰቱ የነበሩትን ግጭቶችና አለመረጋጋቶችን ተከትሎ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ መቀዛቀዝ ማሳየቱን በሚኒስቴሩ የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሪክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ተናግረዋል።

በመሆኑም የተቀዛቀዘውን ዘርፉን ለማነቃቃት የሆቴል ባለቤቶች፣ ቱር ኦፕሬተሮች፣ የመጠጥ አምራች ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ተጋባዥ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ምሁራን የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ ነሐሴ 28 እና 29 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በእለቱም ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡና ከሰባት መቶ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተው የተቀዛቀዘውን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ለመፍጠር የሚያስችሉ ሰፊ ዝግጅቶች መደረጉን አውስተዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ፌዴሪሽን ፕሬዝዳንት አቶ ወርቁ ታምራት ዘርፉ የአገርን ገጽታ ከመገንባት አኳያ ያለው ሚና ሰፊ ቢሆንም በአገሪቷ በቅርብ እየታየ የነበረው ግጭትና አለመረጋጋት በዘርፉ መቀዛቀዝ እንዲፈጠር አድርጎት እንደነበር ጠቁመዋል።

ይህን በመሰለ ጉዳይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከራችን ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣም እሙን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪስት አሶሲሽን ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ በበኩላቸው በቱሪስት መስህብነታቸው ከሚጠቀሱ ግንባር ቀደምት ከተሞች ውስጥ እንደ ባህር ዳርና አዋሳ ባሉ ከተሞች በተፈጠረው አለመረጋጋት የሆቴሎችና ቱሪዝም ዘርፉ መቀዛቀዝ እንደገጠመው ጠቅሰው፤ ምክክሩ ችግር ፈቺ መፍትሄን እንደሚያመጣ መታመኑን ተናግረዋል።