የህዝቡን አብሮነት በማጠናከር የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ እንሰራለን-----የሆሳዕና ከተማ ምክርቤት አባላት

63
ሆሳዕና (ኢዜአ) ነሀሴ 18 ቀን 2011ዓ.ም---በሆሳዕና ከተማ የህብረተሰቡን አብሮነትና እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህል በማጠናከር የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ጠንክረው እንደሚሰሩ የከተማዋ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ጌታቸው ጡሚሶ እንዳሉት በከተማው ሰላም እንዲሰፍን የህዝብ ወኪል ኃላፊነቱ የጎላ ነው። በመሆኑ የወከሉትን ህብረተሰብ ሰላሙ እንዲጠበቅና አንድነቱን እንዲያጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል። ወደ ወከሉት ህብረተሰብ በመሄድ ህዝቡ አንድነቱን እንዲያጠናክር ከማስተማር ባለፈ ለአካባቢ ሰላም ምቹ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል። ለሰላም ዕክል የሚሆኑ ተግዳሮቶች አንስተው ከሕብረተሰቡ ጋር መወያየታቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ በቀጣይም ይህን በማጠናከር ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚሰሩ ገልጸዋል። “የሀገር ሰላም እንዲጠበቅ አካባቢያዊ ሰላም ላይ ይብለጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም” አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ የህዝብን ሰላም በማስጠበቅ ከራስ አልፎ ለሀገር ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ በከተማው ምክር ቤቱ የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙሉነሽ ሴዲሶ ናቸው፡፡ “በተለይ ተተኪው ትውልድ አንድነትንና አርስ በርስ ተቻችሎ የመኖር እሴትን እንዲያጠናክር ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ሙሉነሽ ገለጻ በህብረተሰቡ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀው አብሮነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ወክለው የመጡት ህብረተሰብ ማህበራዊ ግንኙነቱን ከማጎልበት ባለፈ ችግሮች ሲከሰቱ  በሀሳብ ተወያይቶ መፍታት እንዲቻል ህብረተሰቡን የማስተማር ሥራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል። ለሰላም እጦት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድሞ በመነጋገር ለይቶ ለመፍታት እንደሚሰሩና ይህንንም ለማጠናከር ትኩረት ስጥተው እንደሚሰሩ ወይዘሮ ሙሉነሽ ተናግረዋል፡፡ “ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በኩል የድርሻውን እንዲወጣ በማስተማር በኩል  የምክር ቤት አባላት ኃላፊነታችን የጎላ ነው” ያሉት ደግሞ ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል አቶ ስምኦን ኤርጫሞ ናቸው። በቀጣይ ሁሉንም በእኩል የሚያይና ተቻችሎ የሚኖርን ህብረተሰብ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ጠቁመው ፣ በከተማዋ በተለይ ብሔርተኝነትን የሚጸየፍና ለሰላም እና ልማት የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም