በኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎት ምክር ቤት ተቋቋመ

210
ነሀሴ17 / 2011(ኢዜአ) ምክር ቤቱ በክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመራ ሲሆን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተወካዮች አባላት የሚሆኑበትና እስከ ቀበሌ ድረስ የተዋቀረ መሆኑ ተጠቁሟል። ምክር ቤቱ የክልሉ መንግስት፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የተለያዩ የህብረተሰሰብ ክፍሎችን ያካተተ ነው። በክልሉ ጨፌ ምክር ቤት የጸደቀው የዜግነት አገልግሎት ወይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደምብ ከወጣ በኋላ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተሳትፈውበታል። የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ አቅመ ደካሞች የተለያየ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል። አገልግሎቱ በገንዘብ ሲተመን ከ463 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ተናግረዋል። የዜግነት/የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በዋነኛነት ለሁሉም ምቹ የሆነች አገር ለመገንባት፣ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ሁሉም በመተባበር ነገን ዛሬ ላይ ለመገንባት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። በገዳ ስርዓት መሰረት በጎ ተግባራትን ማከናወን አካባቢን ለሁሉም ነዎሪዎች ምቹ ማድረግ፣ የተመናመነ የተፈጥሮ ኃብትን ወደነበረበት ለመመለስ እና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት መሆኑን ጠቁመዋል። የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ባለፉት ወራት በተሰራው አገልግሎት ጥሩ ውጤት መገኘቱንና ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በቀጣይ የዜግነት አገልግሎት አሰጣጡ ከክልሉ የመንግስት ስራ ጋር ተቀናጅቶ እንደሚተገበር ጠቁመዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ ጥሩ ስነ ምግባር ያለው ትውልድ በመገንባት ጠንካራ ክልል እና አገር መፍጠር ያስፈልጋል። በአገልግሎቱ ለህብረተሰቡ የተመቻቻ ድጋፍ መስጠት እንደሚቻል የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ተሳታፊ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ለሰሩት ስራ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸውና የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲፈልጉ ቅድሚያ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። በቀጣይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ ወጣቶች አገልግሎቱን ከክልሉ ባለፈ በሌሎች ክልሎች የሚሰጡበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተናግረዋል። በምክር ቤቱ ምስረታ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች በበኩላቸው በመንግስት ደረጃ ይህ አግልግሎት ስራ ላይ መዋሉን አድንቀዋል። ''አገልግሎቱ በባህላችን የተለመደ ነበር፤ ደምቡ የተቀዛቀዘውን ተግባር ያጠናክራል'' ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የነገ ትውልድ እጣ ፈንታ ዜጎች ዛሬ ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ ይወሰናል” ማለቱ ይታወሳል። በጨፌ ኦሮሚያ ጸድቆ ወደ ስራ የገባው የዜግነት አገልግሎት አዋጅ በገዳ ስርዓት መሰረት የክልሉ ነዋሪዎች በበጎ ፈቃድ በነጻ አገልግሎት የሚሰጡበት አሰራር ሲሆን ዋና ዓላማውም ትውልዱ በገዳ ስርዓት መሰረት ለክልሉ አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ ችሎታና ብቃት ያካበተ እንዲሁም ለአገሩ ፍቅር ያለው ዜጋ እንዲፈጠር ማድረግና ዜጎች ተቋርቋሪ ሆነው አብሮ የመስራት ባህልን እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም