ኢትዮጵያ ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ ብድርን የሚሸከም ኢኮኖሚ መፍጠር እንዳለባት ተገለፀ

68
አዲስ አበባ  ነሀሴ 17 /2011 ኢትዮጵያ ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ ብድርን የሚሸከም ኢኮኖሚ መፍጠርና ወደውጪ የሚላክ ምርትና  አገልግሎትን ማበራከት እንደሚኖርባት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለፁ። ኢትዮጵያ ባለባት የብድር ጫናና ቀጣይ መወሰድ ስላለበት ማስተካከያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ አገሪቱ ከገባችበት የብድር ጫና ለመላቀቅ ወደውጪ የምትልከውን ምርት ማሳደግ እንዳለባት ተናግረዋል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያና አማካሪ ዶክተር በየነ ታደሰ እንዳሉት የተለያዩ የዓለም አገራት በተለያዩ ጊዜያት የብድር ጫና ውስጥ ገብተው ነበር። በአንድ ወቅት ብራዚል ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ ጋር ተቀራራቢ የሆነ የብድር ጫና ገጥሟት እንደነበርና በወቅቱ በመሪዋ አማካኝነት የተደረገ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ችግሯን እንድታቃልል እንደረዳት በማሳያነት ያነሳሉ። "ኢትዮጵያ የተበደረችውን ብድር ላሰበችው ዓላማ አውላ ቢሆን አሁን ያለው የብድር ጫና አይኖርም ነበር" የሚሉት ዶክተር በየነ አገሪቱ ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የተበደረችው ብድር በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋሉን አስረድተዋል። በብድር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥናት ተመስርተው ባለመጀመራቸው ያላለቁ ወይም ጥራት የጎደላቸው በመሆናቸው እነርሱን ለማስጨረስ በራሱ ሌላ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን በመግለፅ። ብድርን ያለመክፈል በርካታ ችግሮችን እንደሚያመጣ የገለጹት ዶክተር በየነ የአገርን ገፅታ የሚያበላሽና የመደራደር አቅምን የሚቀንስ መሆኑን ገልፀዋል። በዓለም ላይ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የብድር ጫና ውስጥ ገብተው እንደነበር ያነሱት የልማት ምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ደረጄ ደጀኔ በበኩላቸው ኢትዮጵያም ከዚህ በፊት በ1980 አካባቢ ከፍተኛ የብድር ጫና ውስጥ ገብታ እንደነበር ያነሳሉ። እናም በወቅቱ በተደረገላት የብድር ስረዛ ዕዳው ቀሎ እንደነበርና ከዛ በኋላ መሰል ችግር የገጠማት በአሁኑ ወቅት መሆኑን ተናግረዋል። በዓለም ላይ እንደ አሜሪካና ጃፓን ያሉ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ አገራት አሁንም ከፍተኛ ብድር ያለባቸው ቢሆንም የሚያሳስበው የብድር ገንዘብ መብዛት ሳይሆን ዕዳውን መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ነው ብለዋል። አቶ ደረጄ ከውጭ ማስመጣት የሚኖርብን ምርቶችን ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለወጪ ንግድ ለማዋል የሚጠቅሙ የማምረቻ መሳሪያዎችን ነው ይላሉ። በቀጣይም የብድር ጫናን ለመቀነስ ወደ ውጭ የሚላክ ምርትን ማሳደግ፣ ብድርን ለማምረቻ መሳሪያዎች ለማዋል መበደርና በመንግስት የተጀመሩ የብድር ጊዜን ማራዘም የመሳሰሉ ተግባራት መጠናከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ምሁራኑ አሁን የተጀመረው ብድርን በረጅምና በአነስተኛ ወለድ የመክፈል ድርድር አጠናክሮ መቀጠል መልካም ቢሆንም ይህም ግን ዕዳን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ በመሆኑ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በድርድር ወደ ዕዳ ስረዛ እንዲቀየር መስራት ይኖርበታል ይላሉ። ህገ-ወጥ ንግድን ለመቆጣጠርና የግብር ገቢን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያስረዳሉ። የሚመረቱ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን የሚተኩ ለማድረግና ወደውጪ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ ምርታማነት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚሰሩ ስራዎችና የመንግስት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደግል የማዘዋወሩ ተግባር ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መከወንም ጠቃሚ መሆኑን መክረዋል። ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ይውላሉ ተብለው የባከነ የብድር ገንዘብን ለማስመለስም በሙስና ገንዘቡን ያባከኑ ሰዎችን በህግ መጠየቅ ያስፈልጋል ይላሉ። የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በኢትዮጵያ ከመጣው ለውጥ በኋላ አገሪቱ የነበረባትን ዕዳ ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ገልጿል። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2015 ዝቅተኛ የውጭ ዕዳ ጫና ስጋት የነበረባት ሲሆን ከ2018 ጀምሮ ከፍተኛ ስጋት ያለባት አገር ሆናለች። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ እንዳሉት የአገሪቱን የብድር ጫና ከከፍተኛ ወደ ዝቅተኛ ስጋት ለማውረድ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወን ቆይቷል። በዚህም የወለድ ምጣኔና የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም የተደረገ ሲሆን ብድር እየተጠየቀ ያለውም የፕሮጀክቶች አዋጪነት ከተጠና በኋላ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የምትበደረውን የብድር መጠንም ለመቀነስ ተችሏል ያሉት አቶ ሀጂ አገሪቱ በ2011 ዓ.ም የተበደረችው ብድር ከ2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር የ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ልዩነት እንዳለው አንስተዋል። ክፍያ እየፈጸመች መሆኑንም ጠቁመዋል። በአገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የታክስ ሪፎርም እየተደረገ ሲሆን ስምንት የታክስ ህግና ደንቦችን ለመተግበር የሚረዱ መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል። የተደረገው ማሻሻያ በአመት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሀጂ ገልጸዋል። መንግስት የብድር ጫናውን ለመቀነስ ከተለያዩ አበዳሪዎች ጋር በመደራደር የንግድ ብድርን በረጅም ጊዜና በአነስተኛ ወለድ ወደሚከፈል መቀየሩን ገልፀው በቀጣይ አገሪቱ የምትበደረው ይኸው አይነት ብድር መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለባት የውጭ ብድር መጠን 27 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም