አገር አቀፉ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ግቡን አሳክቶ ተጠናቋል

94
አዲስ አበባ  ነሀሴ 17 /2011 የመርሃ ግቡሩን መጠናቀቅ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በታላቁ ቤተ መንግስት እየተገነባ ባለው ፓርክ ላይ የችግኝ ተከላ ተካሄዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩያስጀመሩት አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአጠቃላይ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያቀደ ሲሆን፤ ከዚህ መካከል ደግሞ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል ክብረ ወሰን ለመያዝ መታቀዱ ይታወሳል። የመርሃ ግበሩ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የግብርና ሚንስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ በሚገባ ግቡን መትቶ ተጠናቋል። 'ምን ዓይነት ችግኝ በየት ቦታ ተተከለ' የሚለውና ሌሎች ቀሪ መረጃዎች ከተጠናከሩ በኋላ የመርሃ ግብሩ አጠቃላይ ሁኔታ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ነው ያሉት። በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከሉ ውጥን ከእቅድ በላይ መሳካቱን ጠቁመው፤ "በቀኑ ከተተከሉት ችግኞች መካካል 60 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውል ፍራፍሬ የሚሰጡ ናቸው" ብለዋል። በቀጣይ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና ለ2012 ዓ.ም የሚሆን በቂ ችግኝ የማዘጋጀት ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አብራርተዋል። የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትሩ ዶክተር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ትልቅ ነገርን ማሳካት እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ መሆኑን አውስተዋል። በተጀመረው ቁርጠኝነት ልክ ለተከታታይ ጥቂት ዓመታት ችግኞችን መትከል ከተቻለ በጎርፍና ድርቅ የማትጎዳ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ቀላል መሆኑንም ተናግረዋል። አጠቃላይ በሂደቱ ለቀጣይ መሰል ስራዎች የሚሆን ትልቅ ልምድ እንደተቀሰመበት በመጠቆም። እያንዳንዱ ዜጋ የተተከሉ ችግኞችን እንደ ልጆቹ ሊንከባከባቸው እንደሚገባም ዶክተር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ ጥሪ አቅርበዋል። ከችግኝ ተከላ ጎን ለጎን በተለይ በከተሞች አካባቢ የተጀመረውን የጽዳት ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጨምረው ገልጸዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም