ኢትዮጵያና እንግሊዝ የ4 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

104
አዲስ አበባ  ነሀሴ 17 /2011 በኢትዮጵያና እንግሊዝ መንግስታት መካከል የ4 ነጥብ 23 ቢሊየን ብር ድጋፍ ስምምነት ዛሬ አዲስ አበባ ተፈረመ። በገንዘብ ድጋፉ በሚካሄዱት የልማት ተግባራት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያ ተጠቀሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ እና የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ ናቸው። ከእንግሊዝ መንግስት የተገኘው ይህ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ለሚካሄዱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የአካባቢ ንፅህና እና በጤናዉ ዘርፍ ለሚካሄዱ ሌሎች የልማት ውጥኖች ትግበራ የሚውል ነው። ከዚህም ሌላ ገንዘቡ የምግብ እጥረት ችግርን ለመከላከል በሚል የሚካሄደውን የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ለማጠናከርና በአገሪቱ ገጠራማ ክፍል የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንደሚዉልም በስምምነቱ ወቅት ተነግሯል። በዚህም በድርቅ በተጠቁና ተጋላጭ በሆኑ አካባበቢዎች የሚኖር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቀሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለረጅም ዓመታት በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አጋርነት ሲሰሩ መቆየታቸዉን ገልፀዋል። ከዚህ በፊት ለጋራ እድገት የሰሯቸዉ ስራዎች ለሌሎች አገሮች ምሳሌ እንደሚሆንም ተናግረዋል። አገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በማጠናክር ለወደፊት በኢቨስትመንትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሰራሉም ብለዋል። የእንግሊዝ አለም አቀፍ ልማት ሚኒስትሩ ሚስተር አሎክ ሻርማ በበኩላቸው "ከኢትዮጵያ ጋር የመሰረትነው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከሌሎች አገሮች ጋር ካለን ግንኙነት አንፃር ሲታይ ተመራጭ ነዉ"  በማለት ገልፀዋል። በአገራቱ መካከል ያለውን ይህንን የቆየ ግንኙነት በማጠናከርም ወደፊት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚሰሩም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም