በከተማዋ የሚገኙ አፀደ ህፃናት እና 1ኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው

153

ነሐሴ 17/2011 በአዲስ አበባ  የሚገኙ የአፀደ ህፃናት እና የ1ኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ለ2012 የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት እንዳሉት፤ በ2012 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማርን ምቹ ለማድረግ በሁሉም የመንግስት የአፀደ ህፃናት እና የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች እድሳት፣የተማሪዎች ምዝገባ እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራ እየተሰራ ነው።

በሐምሌ ወር የተጀመረው የመማሪያ ክፍሎችን የማስዋብ እና የማደስ እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት ዓመታትም ተመሳሳይ ሥራ የተሰራ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ከመንግስት ከፍተኛ በጀት ተመድቦ በተደራጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ትምህርት ቤቶቹን ምቹ ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በተማሪዎች ላይ አዲስ የመነቃቃት መንፈስ በመፍጠር በመማር ማስተማር ሂደቱ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለፁት።

ከእድሳት ስራው ጎን ለጎንም የተማሪዎች ምዝገባ ከሃምሌ 15-30/2011 ተካሂዶ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች መዝግበው እንዳጠናቀቁ የጠቀሱት አቶ አበበ፤ ምዝገባው ተጠናቆ ትምህርት ቤቶች በሚያቀርቡት የተማሪዎች ብዛት የደንብ ልብሶችንና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ይሟላል ተብሏል።

የኒው ኢራ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወይዘሮ ሩሃማ ታደሰ በበኩላቸው  የተማሪዎች ምዝገባ ማጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቱን ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከእድሳት በተጨማሪም የመመገቢያ አዳራሽ ዝግጅት፣ ቤተ ሙከራዎች፣ የወንበር ጥገና፣ ቤተ መፅሃፍትን ዝግጁ የማድረግ፣ የተማሪዎችን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ አካባቢን የማድረግና ግቢውን የማጠር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን  ነው የተናገሩት።

የመማሪያ አካባቢዎችን ምቹ ማድርግ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ በሻገር የተማሪዎችን ጤንነት ለመጠበቅና የትምህርት ተነሳሽነታቸውን በመጨመር ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክትም ነው ወይዘሮ ሮሃማ የገለጹት።

በ2012 የትምህርት ዘመን እየተደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት በትምህርት ቤቶች አካባቢ ይስተዋሉ የነበሩ  እንቅፋቶችን በማስወገድ፤  የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  ያስችላል ያሉት  ደግሞ የአፄ ፋሲል አፀደ ህፃናት ና 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መሳይ ገላው ናቸው።

በትምህርት ቤቱ የምዝገባ ሂደት መጠናቀቁን ገልጸው፤ዕድሳት ስራውንም በተያዘለት ግዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል  በዚሁ ትምህርት ቤት የወላጅ፣ ተማሪዎችና መምህራን ህብረት ለቅድመ ዝግጅት ስራው ስኬታማነት ከመምህራንና ከተማሪ ወላጆች ጋር በመተባበር በምዝገባ ሂደቱና በሌሎች ተግባራት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን  የተናገሩት የህብረቱ  የዲሲፒሊን ኮሚቴው ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ዘለቀ ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በ2012 የትምህርት ዘመን የምገባ ፕሮግራም እንደሚጀመርም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም