በኢትዮጵያ የዝቃጭ አያያዝና አወጋገድ ላይ አዲስ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

78

ነሀሴ 17/2011በኢትዮጵያ የዝቃጭ አያያዝና አወጋገድ ላይ አዲስ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ እየተዘጋጀ ባለው መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር  ዛሬ በአዲስ አበባ መክሯል።

የኮሚሽኑ  የፖሊሲ፣ ህግና ደረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ አየለ ኤገና እንዳሉት በአገሪቷ እያደገ ለመጣው  ኢንዱስትሪ ተመጣጣኝና በዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተቃኘ መመሪያ ያስፈልጋል።

በዚህም ኮሚሽኑ በዘርፉ ያለውን ስራ ለማሳካት የሚያስችለውን መመሪያ ከጀርመን የልማት ድርጅት (GIZ) ጋር በመተባበር ባለፉት ሁለት ዓመታት እየዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአገሪቷ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ጠቃሚ የሆኑና ያልሆኑ ኬሚካሎች በሰው፣ በእንስሳትና በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ ይገኛሉ።

በተለይም በዝቃጭ አያያዝና አወጋገድ ላይ በቂ ስራ ባለመሰራቱ ላለፉት 30 ዓመታት በአግባቡ ያልተወገዱ  ዝቃጮች እንዳሉም መረጃዎች ያሳያሉ።

በአገሪቷ ከአደገኛ ቆሻሻ፣ ከዝቃጭ፣ ከፍሳሽና ከደረቅ ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሶስት አሰርተ ዓመታት  የወጡ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች አሉ።

መመሪያውም የወጡ ህጎች ደንቦችና ፖሊሲዎች  ይበልጥ ቀላል በሆነ መንገድ እንዲተገበሩ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

መመሪያው ዝቃጩን እንዴት መያዝ እነደሚቻል፣ እንዴትስ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል፣ እንዴት ማስወገድና ተገቢ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዴት እንደሚሰጥበት በዝርዝር የሚያስቀምጥ ነው።

የዛሬው የመጨረሻ ውይይት ከባለድርሻ አካላትና የተለያዩ አስተያየቶችን እንደ ግብዓት ለመጠቀም መሆኑም ተጠቁመዋል።

አገሪቷ በቅርቡ የገነባቻቸው የኢንዱሰትሪ ፓርኮች የዝቃጭ አወጋገድ ላይ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን በውይይቱ ያነሱት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሌሊሴ ነሚ ናቸው።

በተለይም በሀዋሳና በቦሌ የኢንዱስትር ፓርኮች ያሉ ዝቃጮችን ለማስወገድ መመሪያ ባለመኖሩ ለአሰራር መቸገራቸውን ነው የተናገሩት።

አሁን እየተዘጋጀ ያለው መመሪያም ተግባራዊ ሲሆን ቸግሩን እንደሚፈታ ተናግረዋል።