አየር መንገዱ ወደ ታይላንድ እና ቬትናም የጭነት በረራ አገልግሎት ጀመረ

179

ነሀሴ 17/2011የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አንድ ቀን ወደ ታይላንድ ባንኮክ እና ቬትናም ሃኖኢ አዲስ የጭነት በረራ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንደተናገሩት አዲሱ የጭነት አገልግሎት በመንገደኞች አውሮፕላን እየተሰጠ ያለውን የጭነት አገልግሎት ያግዛል።

በኢትዮጵያና በታይላንድ እንዲሁም በቬትናም መካከል የተሻለ ትስስር መፍጠር ብቻ ሳይሆን የአየር መንገዱ መዳረሻ በሆኑ ከ60 በላይ የአፍሪካ አገራት ጋር ትስስር ይፈጥራልም ብለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ አገልግሎቱ ኢትዮጵያ በባንኮክ የአየር ጭነት አገልግሎት በመስጠት  ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር አድርጓታል።

በዚህም ለታይላንድና ቬትናም የወጪ ንግድ ላኪዎች የአየር መንገዱ መዳረሻ የሆኑ ከ60 በላይ የአፍሪካ አገራትን በአንድ ጊዜ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ነው የተባለው።

አገልግሎቱ ከአፍሪካ በተጨማሪ ባንኮክንና ሃኖኢን ከአውሮፓ፣ ኤሲያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካ ጋር ያገናኛል ተብሏል።