ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

102
አዲስ አበባ  ነሀሴ 17 /2011 የምጣኔ ኃብታዊ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ ይሳካ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአሜሪካ መንግስት አስታውቋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ያስመዘገበች ቢሆንም በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ሳቢያ እድገቱ ለተለያዩ አደጋዎች እየተጋለጠ መሆኑን ባለሙያዎች ይነገራል። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብር የመግዛት አቅም መውረድ፣ የእዳ ጫና እና የሥራ አጥነት ምጣኔ ኃብቱ ከተጋረጡበት ፈተናዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ዛሬ ይፋ የሆነውና ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮጀክት እነዚህን ችግሮች በመጋፈጥ የምጣኔ ኃብታዊ እድገቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ዋነኛ ግቡ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይናገር ደሴ ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የተጀመረው ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር በዘርፉ ልማትን በማሳደግ የስራ እድልን ለመፍጠርም ያግዛል ሲሉ ዶክተር ይናገር አመልክተዋል። የአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ የተረጋጋ እንዲሆንና የዜጎች ገቢ እንዲጨምርም ፕሮጀክቱ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይኖር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የምታካሂደው ምጣኔ ኃብታዊ ማሻሻያ ፕሮጀክት እንዲሳካ መንግስታቸው የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በአገራት መካከል ያለውን ምጣኔ ኃብታዊ የትብብር ግንኙነት ማጠናከርና የልምድ ልውውጥ ማድረግ ለልማትና ብልጽግና ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል። ይህም የሁለቱን አገራትና ህዝቦች ግንኙነት እንደሚያጠናክረው አምባሳደሩ ገልፀዋል። በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት ዛሬ ይፋ ለሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮጀክት ትግበራ የሚውል የአራት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደሩ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምጣኔ ኃብት ረገድ በተለይም በመንገድ፣ በትምህርት፣ በጤና መሰረተ ልማት ዘርፎችና በኢንቨስትመንት እያስመዘገበች ያለውን ውጤት አምባሳደሩ እድንቀዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ከአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ከመጡና በጥናትና ምርምር ስራ ከተሰማሩ ፕሮፌሰሮች ጋር በዛሬው እለት ምክክር አድርገዋል። በዚሁ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የልማትና እድገት ምርምር ማዕከል የቡድን መሪ ፕሮፌሰር ሪካርዶ ሁስማን የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ዘላቂ ማድረግ እንዲቻል ምጣኔ ኃብታዊ መሰረቶችን ማስፋት እንደ አንድ ስልት መወሰድ አለበት ሲሉ መክረዋል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረትም ከኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎችና በዘርፉ ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱም ፕሮፌሰር ሪካርዶ ሁስማን አረጋግጠዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም