የጋራ ኮማንድ ፖስቱ ግጭትን በማስቆም በኩል ውጤታማ ሥራ መስራቱን አስታወቀ

780

አሶሳ (ኢዜአ) ነሀሴ 17 /2011  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የአማራ ክልሎች የጋራ ኮማንድ ፖስት በአካባቢው ለወራት የዘለቀውን ግጭት በማስቆም ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

አንዳንድ የመተከል ከተማ ነዋሪዎች ኮማንድ ፖስቱ ሃሰተኛ ወሬን ማስወገድ እና ተፈናቃዮችን ለመመለስ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

የክልሎቹ የጋራ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ አበራ ባዬታ ለኢዜአ እንዳሉት ኮማንድ ፖስቱ በክልሎቹ አጎራባች አካባቢዎች ባለፈው አንድ ወር ባከናወናቸው ሥራዎችን ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በእዚህም በአካባቢው ለወራት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ግጭቱ በተከሰተበት አካባቢ በርካታ ንብረት መዘረፉን ያስታወሱት ሰብሳቢው ንብረት አስመላሽ ኮሚቴ ተቋቁሞ እስካሁን ድረስ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ለማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ንብረት አስመላሽ ኮሚቴ ከገንዘብ በተጨማሪ በጎች፣ ፍየሎች እና ሌሎችንም የቁም እንስሳትን ጨምሮ የቤት ዕቃዎችን የማስመለስ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አበራ ገለጻ፣ በግጭቱ በመተከል እና በአማራ ክልል አዊ ዞኖች ግጭት  የፈጠሩ 169 ግለሰቦች ተይዘው በጊዜ ቀጠሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት  እየታየ ነው።

ኮማንድ ፖስቱ ከ10 ሺህ በላይ ጥይቶች እና ስድስት ህገ-ወጥ የመከላከያ   ልብስ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አብራርተዋል፡፡

“በግጭቱ ከአካባቢያቸው ከተፈናቀሉት መካከል ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን መመለስ ተችሏል” ያሉት ሰብሳቢው ቀሪዎችን የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

አቶ አበራ እንዳሉት አሁንም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና በጦር መሳሪያ የተደራጀ የቡድን ዘረፋ ዋነኛ የአካባቢው ስጋት ነው፡፡

በክልሎቹ ተጎራባች አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ለጸጥታ አካሉ ያደረጉት እገዛ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ነዋሪዎቹ በአካባቢው የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የጀመሩትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

የመተከል ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ግልገልበለስ የሚኖሩትና በሆቴል ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ድርቤ ለማ በበኩላቸው የከተማዋ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችም ወደ ቄያቸው እየተመለሱ መሆኑንም አመልክተዋል።

“ህብረተሰቡ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ በነጻነት እየተገበያየ አይደለም” ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣ በአካባቢው ጥቃት ሊፈጸም ነው በሚል በየጊዜው በሀሰት የሚነዛው ወሬ  ለእዚህ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ባዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች መሳተፋቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዋ በቀጣይ ሃሰተኛ ወሬን ከምንጩ ማስቆም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች ሙሉ ለሙሉ ወደአካባቢያቸው እንዲመለሱ ኮማንድ ፖስቱ ጥረቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባላት የአካባቢውን ባህል ከመረዳት ባለፈ በስራቸው የሃገር ሽማግሌዎችን አካተው ቢሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑም ወይዘሮ ድርቤ ገልጸዋል።

“በግጭቱ ሁላችንም ከመክሰር ያለፈ ያተረፍነው ነገር የለም “ያሉት ደግሞ አቶ ታደለ ኢብሳ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።

በቀጣይ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ያለፈውን በመርሳት በአዲስ መንፈስ መነሳት እንዳለበት አመልክተዋል።

በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አይሲካ ቀበሌ በግለሰቦች መካከል ተከስቶ ለወራት የዘለቀው ግጭት በርካቶችን ለሞትና ለስደት ከመዳረግ ባለፈ ከፍተኛ ንብረት ማውደሙ ይታወሳል፡፡