የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ምርት-ተኮር የቁጥጥር ስርዓት እንደሚተገብር አስታወቀ

69
ነሐሴ 16/2011 የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ስርዓቱን ምርት-ተኮር እንደሚያደርግ አስታወቀ። ባለስልጣኑ የ2011 በጀት ዓመቱን ዕቅድ አፈጻፀምና ለቀጣይ ሊሰሩ ባቀዳቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። ከዚህ በፊት የነበረው ቁጥጥር በምርት ተደራሽነት ላይ በሚሰሩ አከፋፋዮች ነበር። ይህ የቁጥጥር ሂደት የሚፈለገውን ውጤት ባለማምጣቱ የቁጥጥር ስርዓቱ ከአመራረት ጅምሮ እንዲሆን በማድረግ የምግብና መድሃኒት ጥራት ለማምጣት እንደሚሰራ ተገልጿል። በበጀት ዓመቱ ለህብረተሰቡ በሚቀርቡ ምግቦችና መድሃኒቶች ላይ ችግር የሚያስከትሉ ነገሮችን በማስቀረት በአመራረትና በዝግጅት ሒደቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የባለስልጣኑ የምግብ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በትረ ጌታሁን ተናግረዋል። ''በባልትና፣ በቅቤና በማር ምርቶች እንዲሁም አገር ውስጥ ባዕድ ነገሮች ይቀላቀላል'' ያሉት አቶ በትረ፤ አምራች ተቋማት ምርቶቻቸውን ለተጠቃሚው ከማቅረባቸው በፊት በቅድሚያ ጥራቱን እንዲከታተሉ መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም ከህብረተሰቡና ከጸጥታ አካላት ጋር በተደረገ የተቀናጀ ቁጥጥር 2 ነጥብ 15 ቶን ባዕድ ነገሮች የተቀላቀለባቸውን ቅቤ፣ ማርና የባልትና ምርቶች እንዲወገዱ መደረጋቸውን ጠቁመዋል። የጥራት መስፈርቶችን ያላሟሉና አምራች ድርጅቶች ያልታወቁ 110 ምርቶች ህብረተሰቡ እንዳይጠቀምና ከገበያ እንዲወገዱ መደረጉን አቶ በትረ ተናግረዋል። 31 በሚሆኑ የአገር ውስጥ የምግብ አምራች ድርጅቶች ፈቃዳቸው እንዲሰረዝና ምርቶቻቸው ከገበያ እንዲወገድ የማድረግ እርምጃ በባለስልጣኑ አማካኝነት መወሰዳቸውን አመልክተዋል። በቀጣይ የሚዘረጋው የቁጥጥር ስርዓት ስኬታማ እንዲሆን ለማስቻል ከባለስልጣኑ ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች፣ ከማህበረሰቡና ከጤና ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ባለስልጣኑ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በቁጥጥር ስርዓቱ የተገኘውን ስኬት በመጠቀም ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት መመሪያዎችን በማውጣት የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚያካሂድ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም