ድንገተኛ ጥሪ

111
ጌታቸው ሰናይ /ኢዜአ/ እንባዋ ይወርዳል። አካሏ ተጎሳቁሏል። ስሟን ለመናገር አልደፈረችም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመሩት የልዑካን ቡድኑ በሚጓዝበት አውሮፕላን ውስጥ አጠገቧ የተቀመጠው ህጻን በእንባ የተሞላውን የእናቱን ዓይን ትክ ብሎ ይመለከታል። እንባዋ የሰቀቀን ጊዜ አልቆ በደስታ መተካቱን የሚናገር፣ ጥልቅ ሀዘኗን የሚመሰክር ነው። ዓይኖቿ ላይ የሚታየው ስሜት ከ31ዱ ይለያል። ቀርቤ ሳነጋግራት "ስሜን ተወው፤ ይቅርብኝ . . ." አለች። እንባዋ ዱብ ዱብ አለ፤ ሳግ ተናነቃት። “አገኛለሁ ብዬ ከአገሬ ወጥቼ በረሃ ላይ መና ሆኜ ቀርቼ ነበር፤ ከእንግዲህ ከአገሬ መውጣትን ከቶ አላስበውም” አለች፤ በግል ምክንያት ስሟን ለመናገር አልፈለገችም። ትዳሯን በትና ነው የተሰደደችው። የሶስት ዓመት ከሰባት ወር ሕጻን ልጇ ነው ትኩረቴን የሳበው። አብሯት ተሰዶ መከራ የቀመሰው። ትልቅ ሴትም አለቻት፤ አብራት ታስራ የነበረች። እርሷም ከእስር ነጻ ወጥታለች። “አላህ ነው የደረሰልኝ፤ መንግስቴ አለሁልሽ ብሎኛል” በማለት ነው ስሜቷን የገለጸችው። ለደላላ የከፈለችው ሶስት መቶ ዶላር መከራ እንዳመጣባት የተገነዘበችው እስር ቤት ከመግባቷ በፊት በግብጽ በረሃ ለስቃይ በተዳረገችበት ወቅት ነው። መከራዋ አልፎ የአገሯን መሬት ረግጣለች። ተወልዳ ወግ ማዕረግ ወዳየችበት ሐረርም የመሄድ ሃሳብ አላት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ጋር ባካሄዱት የሁለትዮሽ ውይይት ወቅት ከእስር እንዲፈቱ ከተወሰነላቸውና ከተለቀቁት 32 ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ ናት። ሕጻን ልጆቿን ይዛ ለስደት የተዳረገችው ‘የተሻለ ህይወት አገኛለሁ’ በሚል ነበር። በርሃ ውስጥ እስከ አስር ቀን ተቀምጣለች።  መጨረሻ ላይ እርሷና ጓደኞቿ ወደ ግብጽ ሊገቡ ድንበር ሲሻገሩ በአካባቢው ፖሊሶች ተከበቡ። የሀሳባቸው ሳይሳካ በቁጥጥር ስር ዋሉ። በወቅቱ በተተኮሰ ጥይት አንደኛዋ ጓደኛቸው እግሯ ተመታ፤ ቆሰለች። ሌሎች ከተሽከርካሪ ላይ ወድቀው የተጎዱም አሉ። ለአፍታ ዝም ብላ እንባዋን አወረደች “ሶስት ልጆች የነበራት ጓደኛችን ደግሞ በረሃ ላይ ሞተች። አሁን ልጆቿ የት እንዳሉ አናቅም” እልህ በተናነቀው ስሜት አነባች። ከበረሃ መከራና የስቃይ ጉዞ በኋላ እስር ቤት ገቡ። እስር ቤት ውስጥ ምግብ የሚያገኙት በቀን አንድ ጊዜ ነበር። ያውም ስስ ቂጣ። ሌላዋ ተመላሽ ስደተኛ ትግስት ጥበቡ ትባላለች። ከደቡብ  ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ተነስታ ወደ ቤሩት ከዚያም ወደ ግብጽ ከተሰደደች ዓመት ከሁለት ወር ሆኗታል። ሶስት መቶ ዶላር ለደላላ ከፍላለች።  ግብጽ ከገባች በኋላ በግለሰብ ቤት ተቀጥራ ስትሰራ ቆየች። ለስድስት ወር ደመወዝ ሳይከፈላት ሰራች። ደመወዝ ስትጠይቅ “ቆይ” የሚል ምላሽ እያገኘች ጊዜዋን ፈጀች። ስድስት ወር ጨመረች የድካሟን ማግኘት አልቻለችም። ከዚህ በላይ ብዙ መቆየት አልፈለገችም፤ አብራት ከምትሰራው ከአዲስ አበባ ከተሰደደችው ጓደኛዋ ፍሬህይወት ቴኒ ጋር ተያይዛ ጠፋች። የጉልበት ብዝበዛ ትፈጽምባት የነበረችው አሰሪዋ ግን “ዘረፉኝ” ብላ ለፖሊስ አመለከተች። ብዙም ሳይርቁ በፖሊስ ፍለጋ በአምስተኛው ቀን በቁጥጥር ስር ዋሉ። “ከተያዝን በኋላ ወደ እስር ቤት ወሰዱን፤ ለሶስት ቀን መከራ አየን። አራተኛው ቀን ፍርድ ቤት ወሰዱን ሌሎች በተመሳሳይ የታሰሩ ጠበቃ ስለነበራቸው ወጡ፤ እኛ ግን ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ሶስት ዓመት ተፈረደብን። ከዚያም እንደገና አቤቱታ አቅርበን ወደ አንድ ዓመት ዝቅ አለልን። ዘጠኝ ወር ጨርሰናል፤ አሁን። በእግዚአብሔር ተዓምር ዛሬ እዚህ ቦታ ልንገኝ ቻልን” በማለት ነው ጭንቀታቸውን የተናገረችው። ድንገት ነው የተጠራችው። ሁለቱም ያሰቡት ወደ ሌላ እስር ቤት ሊያዘዋውሯቸው እንደሆነ ነው። ግን አልነበረም። ከዚያ ጭንቀት ከበዛበት እስር ቤት መውጣቷ ነው የተበሰረላት። ሁለቱም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በአንድ አውሮፕላን ለመምጣት ዕድል ፈንታ እንደጠራቸው ያወቁት ዘግይተው ነው። “ከእዚያ እስር ቤትና ጭንቅ መውጣታችን እግዚአብሔር እረድቶናል፤ ደርሶልናል። እንደገና የተወለድን መስሎናል። መንግስትን በጣም እናመሰግናል” ይህን ሀሳቧን ፍሬህይወትም ትስማማበታለች። ማይጨው አካባቢ የተወለደው የ25 ዓመቱ አማን ተስፋዬ ለስደት የወጣው ከአዲስ አበባ ነው። ከአገሩ ሲወጣ ሰርቶ ለማደርና ለመለወጥ አስቦ ነው። ከአዲስ አበባ ተነስቶ ግብጽ ከመግባቱ በፊት ለአራት ወር ተቀምጧል። ሊቢያ ተሻግሮ ስምንት ወር ታስሯል። ከዚያ ስቃዩ ሲበዛባቸው ከጓደኞቹ ጋር ጠፍቶ ወደ ግብጽ ገባ። “የግብጽ ወታደር ያዘን። ሕይወታችን በመትረፉ ዕድለኞች ነን፤ ከእንግዲህ ቢከፋኝም ቢደላኝም፤ አገሬ ይሻለኛል” ያለው አማን አንድ ዓመት በግብጽ እስር ቤት ቆይቷል። ዳግም ላለመሰደድ ቁርጠኛ አቋም መያዙን ከንግግሩ መረዳት ይቻላል። መንግስት ዜጎቹን በማስፈታቱ “በእጅጉ አመሰግናለሁ” በማለት ነው ስሜቱን የገለጸው። ሌላው በስደት ግብጽ የገባችው ማወርድ ሱፍያ ኡመር ናት። በሱማሌ ብሄራዊ ክልል ውስጥ በነርስነት ስታገለግል ቆይታለች። ገና ወጣት በመሆኗ ሰርቼ ጥሪት ላፍራ በማለት ወደ ግብጽ ተሰድዳለች። ነገር ግን እዚያ የገጠማት አስደንጋጭ ነገር ነው። መንገድ ስትሻገር ተሽከርካሪ ገጫት። በዚህም ሆስፒታል ገባች። ህክምና ስትከታተል ቆየች። እግሯ ላይ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላት በጀሶ ታሽጓል። ስቃይ ይሰማታል። ምንም ጥሪት ባልያዘችበት ሁኔታ ራሷን ሆስፒታል ውስጥ አገኘች። “ህክምናዬን አገሬ ውስጥ መከታተል ይሻለኛል” ነው ያለችው እያነባች። ተሰደውና በሰው አገር በእስር ቤት ሲሰቃዩ ቆይተው የተመለሱት እንዴት ከእስር ለመውጣት እንደቻሉ መጀመሪያ አካባቢ ግምት አልነበራቸውም። በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሲሳፈሩ ከማን ጋር? እንዴት? እንደሚሄዱ አያውቁም፤ አገራቸው ለመግባት ከመጓጓትና እውነቱን በጥርጣሬ ከመመልከት በቀር ስለክስተቱ አልተረዱም። ድንገት ካሜራና ቪዲዮ ሲመለከቱ ግራ ተጋቡ። በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ወደ እነርሱ ሲቀርቡ ያልጠበቁት ክስተት ነበርና ተደነቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ለአገራችሁ አበቃችሁ” በማለት በመፈታታቸው የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹላቸው በግርምት እያዩ ደቂቃዎችን አሳለፉ። ሁሉም ስሜት እየተናነቃቸው ምስጋናቸውን አቀረቡ። የደስታ እንባ ያነቡ፤ በፈገግታ ስሜታቸውን የገለጹ ነበሩ። ፎቶ መነሳት እንደሚችሉ ሲነገራቸው በስሜት የፈነደቁም ብዙዎች ናቸው። ባልጠበቁት ድንገተኛ ጥሪ፤ እንደፈሩት ሌላ እስር ቤት ሳይሆን አገራቸው በክብር ገቡ፤ ያውም ከአገሪቱ መሪ ጋር-በአንድ አውሮፕላን።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም